ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የህወሓት ተዋጊዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቀረቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, fbc

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከህወሓት ጎን የተሰለፉ ተዋጊዎች በሙሉ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረባቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

ባለፈው ሳምንት ከአማጺያኑ ጋር የሚደረገውን ፍልሚያ በጦር ግንባር በመገኘት እንደሚመሩ አሳውቀው ወደዚያው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሠራዊቱ መሪዎች ጋር መምከራቸው ተገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ ከህወሓት ጋር ተሰልፈው የሚገኙ ተዋጊዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት እጃቸውን በመስጠት ራሳቸውን እንዲያተርፉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን "የትግራይ ወላጆችም ልጆቻችን የት ደረሱ" ብለው እንዲጠይቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነቱ በሚካሄድበት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚገኙ የጦር ግንባሮች መካከል በአንደኛው ተገኝተው የዘመቻ የመጨረሻ ዕቅድ ላይ እንደመከሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በማኅበራዊ ገጹ ላይ አመልክቷል።

የአማጺያኑ ተዋጊዎች በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚካሄደው ዘመቻ በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ መስዋዕትነት ድል የሚረጋገጥበትን መመሪያ መስጠታቸውን ጨምሮ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላምና ልማት ነው። ማወደእዚህ ጦርነት የገባነው ተገድደን ነው። ማሸነፋችን ግን አይቀሬ ነው" ማለታቸውም ተዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በማቅናት የጦርነቱን ሂደት በመምራት መሳተፍ መጀመራቸው ከተገለጸ ከቀናት በኋላ የመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ግንባሮች በወሰደው እርምጃ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ስፍራዎችን ማስለቀቅ መቻሉ ተዘግቧል።

ከእነዚህም መካከል የአፋርና የአማራ ክልል አዋሳኝ የሆነችው ቁልፍ ከተማ ጭፍራን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባቷ ተዘግቧል።

ይህንንም ተከትሎ የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንትው ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እየተመራ ያለውን ጦር አጣጥለው የትግራይ ኃይሎች ማዕከላዊ ዕዝ "በመሬት ላይ ስላለው ሁኔታ ግምገማ በማድረግ በቀጣይ ስለሚካሄደው ማጥቃት ውሳኔ ሰጥቷል" ብለዋል።

እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ዝርዝር መረጃ መግኘት ባይቻልም በተለያዩ ግንባሮች በመከላከያ ሠራዊትና በአማጺያኑ መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ ይነገራል።

አንድ ዓመት ያለፈው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት በአሁኑ ጊዜ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱ ይነገራል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ እንዳለው ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 9.4 ሚሊዮን ደርሷል።