የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ኮምቦልቻ እና ላሊበላ የሰብዓዊ እርዳታ በረራ መፍቀዱን ገለጸ

ሐምሌ አጋማሽ ላይ የረድኤት ድርጅት ሠራተኖች በሰብዓዊ እርዳታ በረራ በትግራይ መዲና መቀለ በደረሱ ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, WFP

የምስሉ መግለጫ, ሐምሌ አጋማሽ ላይ የረድኤት ድርጅት ሠራተኖች በሰብዓዊ እርዳታ በረራ በትግራይ መዲና መቀለ በደረሱ ጊዜ

የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሓት ቁጥጥር ሥር ወደሚገኙት ኮምቦልቻ እና ላሊበላ ከተሞች የሰብዓዊ እርዳታ በረራ እንዲካሄድ መፍቀዱን አስታወቀ።

ከዚህ በተጨማሪ 369 እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ ፍቃድ መስጠቱንም ገልጿል።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጠቅሶ ወደ ሁለቱ ከተሞች የሰብዓዊ እርዳታ በረራ እንዲሁም ወደ ትግራይ የእርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ጉዞ ፍቃድ ተሰጥቷል ብሏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ከሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን ጋር ትላንት ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው ስለ እርዳታ ጉዞ መፈቀድ የተናገሩት።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ እና ፌልትማን የሰሜኑን ጦርነት መግታት ስለሚቻልባቸው መንገዶች የተወያዩ ሲሆን፤ ይህም የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ መድረስን ያካትታል።

የላሊበላ ከተማ ለወራት በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ስትሆን፤ የኮምቦልቻ ከተማ ደግሞ ከሳምንታት በፊት በህወሓት አማጺያን ቁጥጥር ሥር መግባቷ ይታወሳል።

ጦርነቱ እጅግ መፋፋሙ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን የበለጠ እንደሚያስተጓጉል የተባበሩት መንግሥታት መግለጹ አይዘነጋም።

በተለይም በላሊበላ በርካታ ነዋሪዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸው ሲነገር ቆይቷል።

በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲጠብቁ እንዳስገደዳቸው የገለጸው የመንግሥታቱ ድርጅት፤በሰሜን ኢትዮጵያ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር ወደ 7.1 ሚሊዮን መጠጋቱን አስታውቋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኢያሱ መስፍን፤ በህወሓት አማጺያን ለወራት ተይዘው በሚገኙ አካባቢዎች ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ምንም ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ አለመደረጉን ለቢቢሲ መግለጻቸው አይዘነጋም።

በሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ እና ሌሎች አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ ባለመድረሱ በመድኃኒትና በምግብ እጥረት ሳቢያ የሰዎች ሕይወት እያለፈ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ መዲና መቀለ በተከታታይ የአየር ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎችን ለማቆም ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት አማጽያን በበኩላቸው አንዳቸው ሌላቸውን የእርዳታ ጉዞን በማሰናከል ይከሳሉ።

ህወሓት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመምጣት እንደ ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ የሚጠይቀው ይገኝበታል።

አዲስ አበባ የሚገኙት የአፍሪካ ሕብረት የምሥራቅ አፍሪካ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከሚወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጉዳይ አንዱ ነው።

ለጦርነቱ መፍትሔ የሚሉትን ሐሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያብራሩ የሚጠበቁት ኦባሳንጆ፤ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጉዳይም እንደሚያነሱ ከመንግሥት ኮምንኬሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

ከሰሞኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የሚውል 40 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ኃላፊ የሆኑት ማርቲን ግሪፊትስ፤ በኢትዮጵያ ሕይወት አድን የሰብአዊ እርዳታዎችን ለማከናወን እና ንጹሃን ዜጎችን ለመጠበቅ ከማዕከላዊ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፈንድ 25 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ተናግረዋል።

ከዚህ የሰብአዊ እርዳታ ፈንድ በተጨማሪ 15 ሚሊዮን ዶላር የቀረበ ሲሆን፤ በጠቅላላው በኢትዮጵያ ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት 40 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚሆን ተገልጿል።