ፌልትማን ጦርነቱ ስለሚገታበት መንገድ ከምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ጋር ተነጋገሩ

ጄፍሪ ፌልትማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ የሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው ጦርነቱን መግታት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ።

እስካሁን ድረስ ስለ ፌልትማን እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ውይይት ይዘት ዝርዝር መረጃ ባይወጣም፤ ሮይተርስ የዜና ወኪል የተኩስ አቁም ላይ መድረስን ጨምሮ ሌሎችም ጦርነቱን ማቆም ስለሚቻልባቸው መንገዶች መነጋገራቸውን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በበኩሉ፤ ፌልትማን ጦርነቱ እንዴት መገታት እንዳለበት የአገራቸውን አቋም ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል ሲል ዘግቧል።

የአሜሪካ መንግሥት ተዋጊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ እና ለተጎጂዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል።

አቶ ደመቀ በበኩላቸው የህወሓት ኃይሎች ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች እንዲወጡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና መደረግ እንዳለበት በመግለጽ የኢትዮጵያን አቋም ለፌልትማን ማስረዳታቸውን ኢዜአ ጨምሮ ዘግቧል።

ፌልትማን በዚህ ዙር ጉብኝታቸው ለሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ቆይታ የሚያደርጉ ሲሆን ከሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በጦርነቱ ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

ፌልትማን ከኅዳር 9 እስከ ኅዳር 11/2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣናትን እንዲሁም ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ወኪሎችን እንደሚያነጋግሩ ተገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ፌልትማን ጦርነቱ የሚገታበትን መንገድ በማፈላለግ ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል።

"ጦርነቱ ድርድርን ተመርኩዞ ስለሚቆምበት ሁኔታ፣ እንዲሁም ግጭቱ በዘላቂነት እንዴት ሊቆም እንደሚችል ይወያያሉ" ሲል መግለጫው አትቷል።

"በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እና የሰዎችን ሕይወት የሚያድን ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ ማስቻል የአሜሪካ ፍላጎት ነው" ሲልም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አክሏል።

ትላንት አዲስ አበባ ላይ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ጄፍሪ ፌልትማን "ጦርነቱን አቁሞ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት አጠናክረው ቀጥለዋል" ብለዋል።

ኦባሳንጆ ወደ አዲስ አበባ መመለስ

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አድርጎ የሾማቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆም በድጋሚ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ኢትዮጵያ ገብተዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር የተገናኙት የአፍሪካ ሕብረት ልዑኩ ኦባሳንጆ፤ ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መፍትሔ በማበጀት ረገድ የደረሱበትን ምክረ ሐሳብ ኢትዮጵያ እየጠበቀች እንደሆነ አምባሳደር ዲና በትላንትናው መግለጫቸው ጠቁመዋል።

ኦባሳንጆ ቀደም ሲል ባደረጉት ውይይት የፌደራሉን መንግሥት ባለሥልጣናት እና የህወሓት መሪዎችን ካነጋገሩ በኋላ በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለውን ፍላጎት ለመረዳት የሚያስችል መረጃ እንዳገኙ መግለጻቸው ይታወሳል።

ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ መሰጠት እንዳለበትም ኦባሳንጆ ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ትናንት በማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ ኦባሳንጆ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ጠቅሶ፤ ልዑኩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተገናኝተው መፍትሔ በማፈላለግ ሂደታቸው የደረሱበትን ሐሳብ ይገልጻሉ ብሏል።

በተጨማሪም ኦባሳንጆ እያደረጉት ስላለው ሰላም የማምጣት ጥረት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ ሕብረት አምባሳደሮች ማብራሪያ እንደሚሰጡም ይጠበቃል።

አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት እንዲያበቃ ለማድረግ የአፍሪካ ሕብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎች አገራት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ግፊት እኣደረጉ ይገኛሉ።