አሜሪካ በኤርትራ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የጣለችወን ማዕቀብ ኤርትራና ኢትዮጵያ ተቃወሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት በስድስት የኤርትራ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣሉን ተከትሎ እርምጃውን የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ተቃወሙ።
የአሜሪካ የፌደራል ግምጃ ቤት አርብ ምሽት ይፋ እንዳደረገው ማዕቀቡ የኢትዮጵያን መረጋጋትና አንድነት እያናጋ ነው ባለው ቀውስና ግጭት ውስጥ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን ስድስት የኤርትራ ተቋማትና ዜጎች ላይ የተጣለ መሆኑን አመልክቷል።
ዕቀባው የተጣለባቸው ሁሉም ከኤርትራ መንግሥትና ከአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ጋር የተያያዙ ተቋማትና ግለሰቦች ሲሆኑ፤ እነሱም የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ (ህግዴፍ)፣ ህድሪ ትረስት እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን፤ ግለሰቦቹ ደግሞ አብረሃ ካሳ ነማሪያም እና ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን የተባሉት ናቸው።
ይህንንም ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት በተቋማቱና በዜጎቹ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አሜሪካ ቀደም ሲል ከኤርትራ አንጻር ስትከተለው የነበረው "የተጻራሪነት ፖሊሲ ተከታይ ነው" በማለት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል ባወጣው መግለጫ ተቃውሞታል።
በአሜሪካ አስተዳደር የተጣለው ማዕቀብ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚቃረን፣ የአገሪቱን ሉአላዊነት እንዲሁም የሕዝቡንና የመንግሥቷን ነጻነት የጣሰ ነው በማለት፤ ይህ እርምጃ በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ዘላቂ መረጋጋት ለማምጣት እንቅፋት በመሆን ቀጣይ ቀውስን ያስከትላል ብሏል።
የኤርትራ መንግሥት "ሕገ ወጥ እና ከሞራል ያፈነገጠ" ያለው ማዕቀብ የኤርትራን ሕዝብ አይጎዳም ቢባልም "በሕዝቡ ላይ ረሃብና ስቃይን በማስከተል ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ብጥብጥን ለማስከለተል ያለመ ነው" በማለት የአሜሪካ አስተዳደርን እርምጃ አጥብቆ ተቃውሟል። ለሰላምና ለፍትህ የቆሙ ኃይሎች ድጋፋቸውን እንዲሰጡም ጥሪ አቀርቧል።
በኢትዮጵያ ባለው የሰብአዊ እርዳታ እና የሰብአዊ መብት ቀውስ እንዲሁም ጦርነት ምክንያት ባለፈው መስከረም ወር ላይ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተፈረመውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መሠረት አድርጎ የአሜሪካ የግምጃ ቤት የውጪ ንብረቶች ቁጥጥር ጽህፈት ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀብ መጣሉን አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ምላሽ
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ባወጣው መግለጫ አሜሪካ በኤርትራ መንግሥት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያሳለፈችውን ውሳኔ ተቃውሞ፤ የአሜሪካ እርምጃ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ጠቃሚ ጉዳዮችን ከግንዛቤ ያልከተተ ነው ብሏል።
ለዚህም ህወሓት በሉአላዊት አገር ኤርትራ ላይ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙንና ለዚህም ኤርትራ በደኅንነቷ ላይ ለተደቀነው አደጋ ምላሽ መስጠቷ ሉአላዊ መብቷ መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም የኤርትራ ሠራዊት ወደ ግዛቱ መግባቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምንም አይነት ቅሬታ አለማቅረቡንና እንዲህ አይነቱን ቅሬታ ማቅረብ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ የሌላ አገር አይደለም ሲል የኤርትራ መንግሥት ሠራዊትን በሚመለከት የሚቀርበውን ትችት ተቃውሞታል።
ጨምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት ሠራዊቱን ከኢትዮጵያ ማስወጣቱን በመግለጫው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ በአገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን እንቅፋት ናት ብሎ እንደማያምን በመጥቀስም "በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ላለው ሰላም ስጋት የሆነው ህወሓት ነው" በማለት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ህወሓትን ለማውገዝ ቸልተኛ በመሆኑ በድርጊቱ እንዲገፋበት አድርጎታል ብሏል።
የማዕቀቦች ግብ ሰላምን የሚያናጉ አካላትን ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ለማስገደድ ያለመ ከሆነ "በአሜሪካም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሚወሰዱ ጠንካራ እርምጃዎች ትክክለኛው ኢላማ መሆን ያለበት ህወሓት ነው" በማለት በኤርትራ ላይ የተጣለውን ዕቀባ ተቃውሞታል።
የአሜሪካ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ የኤርትራ መንግሥት እና ተቋማቱ የጎላ ተሳትፎ አላቸው በማለት ማዕቀቡን የጣለ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም በአገሪቱ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።
የአሜሪካ መንግሥት የግምጃ ቤት እና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች በጦርነቱ በመሳተፍ አገሪቱ እንዳትረጋጋ በማድረግ እና ግጭቱን በማባባስ ሰላማዊ መፍትሄ እንዳያገኝ እንቅፋት በሚሆኑ ወገኖች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዳቸውን እንሚቀጥሉ አሳውቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሁን በስድስት የኤርትራ መንግሥት ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የተጣለው ማዕቀብ ያተኮረው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ቀውስ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ ባላቸው ላይ እንጂ በኤርትራ ሕዝብ ላይ አይደለም ብሏል።
አሁን በአሜሪካ ግምጃ ቤት በኩል የተጣለው ማዕቀብ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከህወሓት ጋር ተያያዥ የሆኑ አካላትን ያልነካው ጦርነቱን በውይይት ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤት ያመጡ እንደሆን ለማየት ጊዜ ለመስጠት በማሰብ ነው ብሏል።
ነገር ግን በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት ወገኖች ለሰላማዊ መፍትሄ የሚበጅ ትርጉም ያለው እርምጃ የማያሳዩ ከሆነ አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደምትጥል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አሳውቋል።












