በሶማሌ ክልል የታሰሩት አራት ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ነበድ ቲቪ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Nabad tv

በሶማሌ ክልል መሰረቱን ያደረገው ነበድ የቴሌቪዢን ጣቢያ ከቀናት በፊት መዘጋቱን ተከትሎ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የጣቢያው አራት ጋዜጠኞች አርብ ኅዳር 03/2014 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀረቡ።

በቀድሞዋ የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ፊልሰን አብዱላሂ ባለቤትነት ስር እንደነበረ የሚነገረው ነበድ ቴሌቪዢን ጣቢያ የተዘጋውና ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ባሰራጨው ፕሮግራም ይዘት ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።

በቁጥጥር ስር ያሉት ጋዜጠኞች ኢብራሂም ሁሴን፣ ሰልማን ሙክታር፣ ሙሐመድ ቃሲም እና ሂርሲ ሞሐመድ ሲሆኑ በፖሊስ የተያዙት ኅዳር 01/2014 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ ከቴሌቪዥን ጣቢያው እንደሆነ የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማኅበር ለቢቢሲ ገልጿል።

በዕለቱ የቴሌቪዢን ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ብሎም የጣቢያው ባለቤት እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞዋ ሚኒስትር ፊልሰን አባት በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ሲሆን በማግስቱ መለቀቃቸው ተገልጿል።

አራቱን ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ያቀረበው የክልሉ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ችሎቱን መጠየቁን ተከትሎ የ10 ቀናት ቀጠሮ ሰጥቷል።

የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማኅበር ለቢቢሲ በላከው ደብዳቤ ላይ እንዳስታወቀው አራቱ ጋዜጠኞች ምርመራ ላይ እንደሚገኙ ከጂግጂጋ ከተማ ፖሊስ ነበር የተረዳው።

ጋዜጠኞቹ ከታሰሩ በኋላ ስለ ደኅንነታቸው ለማጣራት ወደታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ መሄዱን የገለጸው ማኅበሩ "በተጠረጠሩበት ወንጀል ዙሪያ ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ ፖሊስ ነግሮናል። በተጨማሪም ፖሊስ በማግስቱ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ አስታውቆናል" ሲል ገልጾ ነበር።

የቴሌቪዥን ጣቢያው መዘጋትንና የጋዜጠኞቹን መታሰር ተከትሎ ማኅበሩ በመላው አገሪቱ የተጣለው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ "የፕሬስ ነጻነትን ለመግፈፍ እንዳይውል" ጥሪውን ያቀረበ ሲሆን በእስር ላይ ለሚገኙት ጋዜጠኞችም አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።

ጋዜጠኞቹን ለእስር ብሎም ጣቢያውን ለመዘጋት የዳረገው አንድ ፕሮግራም መሆኑን የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማኅበር መሪ የሆነችው አያን ሹክሪ ኦስማን ለቢቢሲ በመግለጽ "እንደ ጋዜጠኞች ማኅበር ለአንድ ፕሮግራም በሚል ጣቢያውን መዝጋት ብሎም ጋዜጠኞቹን ማሰር አግባብ ነው ብለን አናምንም" ብላለች።

መንግሥት ጣቢያውን ከመዝጋቱ ብሎም ጋዜጠኞቹን ከማሰሩ በፊት ሌሎች ሊከተላቸው የሚገባ የሕግ ሥርዓቶች እንደነበሩ እና አሁንም ጉዳዩን በአስተዳደራዊ ሂደት መፈታት እንዳለበት አያን ተናግራለች።

ጋዜጠኞቹን ጠርቶ ማናገር፣ የደብዳቤ ማስጠንቀቂያ ወይም ለፕሮግራሙ ማረሚያ እንዲሰራ ማድረግ መቅደም እንደነበረበት ማኅበራቸው እንደሚያምን መሪዋ ገልጻለች።

"ይህ እርምጃ በክልሉ እየተሻሻለ የመጣውን የነጻ ሚዲያ መስፋፋት ያቀጭጫል። መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት እንዲያከብር፣ የታሰሩት ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ብሎም ጣቢያው ወደ ሥራው እንዲመለስ እንጠይቃለን" ስትል አያን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ቢቢሲ ለጣቢያው መዘጋት እና ለጋዜጠኞቹ መታሰር መነሻ የሆነውን ፕሮግራም ይዘት የተመለከተ ሲሆን፤ ፕሮግራሙ የሕዝብ አስተያየት የተሰበሰበት የክልሉ ተወላጆች በሌላው የአገሪቱ ክፍል ስላላቸው ተሳትፎ እና ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ዜጎች በሶማሌ ክልል ስላላቸው ሚና የሚያወሳ ነው።

በቴሌቪዥን ጣቢያው ላይ ለተወሰደው እርምጃ እንዲሁም ለጋዜጠኞቹ መታሰር ምክንያቱ በተጠቀሰው በፕሮግራም ውስጥ የተካተቱት መልዕክቶች ሳይሆኑ እንዳልቀረ ይገመታል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው በክልሉ ያለ ብቸኛው የግል ጣቢያ ሲሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት ተመስርቶ በሶማሌ ክልልና በዙሪያው ባሉ ሶማልኛ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ትኩረት ያደረገ ነው።