አሜሪካ ዕቀባ የጣለችባቸው ስድስቱ የኤርትራ ተቋማት እና ዜጎች እነማን ናቸው?

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት በአራት የኤርትራ ተቋማትና በሁለት ኤርትራውያን ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታወቀ።

የአሜሪካ የፌደራል ግምጃ ቤት አርብ ምሽት ይፋ እንዳደረገው ማዕቀቡ የኢትዮጵያን መረጋጋትና አንድነት እያናጋ ነው ባለው ቀውስና ግጭት ውስጥ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን የኤርትራ ተቋማትና ዜጎችን ኢላማ ያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

የአሜሪካ የግምጃ ቤት የውጪ ንብረቶች ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ባለፈው መስከረም ወር ማብቂያ ላይ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተፈረመውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መሠረት አድርጎ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመጣው ሰብአዊ እርዳታ እና የሰብአዊ መብት ቀውስ እንዲሁም በተባባሰው ጦርነት ሳቢያ እርምጃውን መውሰዱን አሳውቋል።

በዚህም መሠረት ዕቀባው የተጣለባቸው የኤርትራ ተቋማትና ዜጎችን ዘርዝሯል። ተቋማቱ የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ፣ ህድሪ ትረስ እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ሲሆኑ ግለሰቦቹ ደግሞ አብረሃ ካሳ ነማሪያም እና ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን የተባሉት ናቸው።

የግምጃ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የተጣለው ማዕቀብ በኤርትራ መንግሥትና በገዢው ፓርቲ ላይ እንጂ የኤርትራን ሕዝብን የሚመለከት አለመሆኑን ጠቅሶ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ውጤት የማያመጣ ከሆነ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጿል።

በትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉም ኃይሎች ችግሩን በውይይት እንዲፈቱ አሜሪካ ስትጠይቅ የነበረ ሲሆን በተለይ ኤርትራ ሠራዊቷን በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች።

ከወራት በፊት የጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በሁሉም ወገኖች ከፍተኛ አመራሮች ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን አሳውቃ ነበር። አስከትላም የኤርትራ የመከላከያ ኃይል ኤታማዦር ሹም በሆኑት በጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

አሁን በአሜሪካ ግምጃ ቤት አማካይነት የተላለፈው የማዕቀብ ውሳኔ በዋናነት ትኩረት ያደረገው የኤርትራ መንግሥትንና ገዢው ፓርቲ ላይ ነው። አራቱ ተቋማት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከአገሪቱ መንግሥትና ከህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ሁለቱ ግለሰቦችም ቢሆኑ በቀጥታ ከመንግሥት እና ከፓርቲው ጋር የተገናኙ መሆናቸውን የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው መግለጫ አመለክቷል።

የኤርትራ መከላከያ ኃይል

የኤርትራ መከላከያ ኃይል የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ሲሆን በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ዘረፋዎች፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የሰላማዊ ሰዎች ግድያና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ማደናቀፍን የተመለከቱ በርካታ ሪፖርቶች በቀረቡበት ወቅት በስፍራው ይንቀሳቀስ ነበር።

የኤርትራ መከላከያ ኃይል በአሜሪካ መንግሥት የዕቀባ ዝርዝር ውስጥ የተካተተው እንደ ተቋምና አባላቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበራቸው እንቅስቃሴ በቀውሱ ውስጥ ተሳታፊ በመሆን እንዲሁም ግጭቱን ለመፍታት የተኩስ አቁም እንዳይደረግ ወይም ሰላማዊ ሂደት እንዳይኖር በማደናቀፍ መሆኑ ተጠቅሷል።

ህዝባዊ ግንባር ለዴክራሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ)

በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ) በኤርትራ ውስጥ ብቸኛው ሕጋዊ ፓርቲ መሆኑን የአሜሪካ ግምጃ ቤት በመግለጫው አመለክቷል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በቀጥታ የአገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያዝዛሉ፣ ይቆጣጠራሉ፣ በቀጥታ ለኤርትራ መከላከያ ኃይል ጄነራሎች ትዕዛዝ ይሰጣሉ። ይህም ጦር ኃይሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ ባለው ሚና ዋነኛው ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብሏል።

በዚህም ምክንያት ፓርቲው ህግዴፍ እንደ ፓርቲ ወይም አባላቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ቀውስ ውስጥ ባላቸው ሚና ወይም ተኩስ አቁም እንዳይደረግና ችግሩ በሰላም እንዳይፈታ በማደናቀፍ በማዕቀቡ ውስጥ ተካቷል።

አብረሃ ካሳ ነማሪያም (ካሳ)

አብረሃ ካሳ ነማሪያም (ካሳ) የኤርትራ ብሔራዊ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ናቸው። በዚህ ዕቀባ ውስጥ የተካተቱት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተጀመረበት ወይም እየተካሄደ ባለበት ወቅት በነበራቸው የመሪነት፣ የባለሥልጣንነት፣ የከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚነት ወይም በኤርትራ መንግሥት ወይም በፓርቲው ውስጥ አመራር አባል በመሆናቸው ነው።

በዚህም በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ቀውስ ውስጥ በማንኛውም ተግባራት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመሳተፍ ወይም ለመሳተፍ በመሞከር አስተዋጽኦ ነበራቸው በሚል መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

ህድሪ ትረስት (ህድሪ)

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ህድሪ ትረስት (ህድሪ) የተባለው ድርጅት በኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህግዴፍ የተመሰረቱ ሁሉንም የንግድ ተቋማት በስሩ ያቀፈ ነው።

በማዕቀብ ውሳኔው ውስጥ የተካተተውም የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ አንድ ክፍል ወይም መጠቀሚያ በመሆን በኤርትራ መንግሥት ወይም በፓርቲው የባለቤትነት ቁጥጥር ስር በመሆኑ ነው።

ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን (ገብረሕይወት)

ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን (ገብረሕይወት) ለኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህግዴፍ የምጣኔ ሀብት አማካሪ እና የሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

ግለሰቡ በማዕቀቡ ውስጥ የተካተቱት የቁሳቁስ ድጋፍ ወይም የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሸቀጦች፣ የአገልግሎቶችና ሌሎችም አቅርቦቶች ለገዢው ፓርቲ በማቅረብ ነው።

የሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን

የሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን የህግዴፍን ንብረቶችና ገንዘብ የሚያስተዳድር ሲሆን ለፓርቲው ገንዘብ የሚያቀርብ እና የንግድ ድጋፍንም የሚሰጥም ነው።

ኮርፖሬሽኑ ማዕቀብ ውስጥ የተካተተው በገብረሕይወት ባለቤትንት ወይም ቁጥጥር ስር ያለ በመሆኑ ነው ብሏል የአሜሪካ ግምጃ ቤት።

ውሳኔው ምን ያስከትላል?

የአሜሪካ መንግሥት ግምጃ ቤት ይፋ ባደረገው የዕቀባ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ሁሉም የኤርትራ መንግሥት እና ገዢ ፓርቲ ህግዴፍ ተቋማትና ዜጎች ናቸው።

በማዕቀቡ ሳቢያ በተጠቀሱት ተቋማትና ግለሰቦች ስም በአሜሪካ ውስጥ ወይም በአሜሪካዊ ይዞታ ወይም ቁጥጥር ስር ያሉ ሁሉም ንብረቶችና ጥቅሞች እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ሲሆን፤ ይህም ውሳኔውን ለሚቆጣጠረው የግምጃ ቤቱ ክፍል ሪፖርት እንዲደረጉ አዟል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

በአሜሪካ ግምጃ ቤት በኩል የተጣለውን ማዕቀብ አስመለክቶ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጡት መግለጫ እርምጃው የተወሰደው መስከረም አጋማሽ ላይ በፕሬዝዳንት ባይደን የተፈረመውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቅሷል።

ጨምሮም የኤርትራ ኃይሎች በጦርነቱ በመሳተፍ አገሪቱ እንዳትረጋጋ በማድረግ እና ግጭቱን በማባባስ መፍትሄ እንዳያገኝ እንቅፋት ከመሆናቸው በተጨማሪ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈፀማቸውን ተአማኒ ሪፖርቶች አሉ ብሏል።

በግጭቱ የሚሳተፉት ሁሉም ወገኖች የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች አሜሪካንን በጽኑ እንደሚያሳስባት የገለጸው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ፣ አሁንም የኤርትራ ኃይሎች በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል።

እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም በአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኩል የሚደረገውን ጥረት አሜሪካ እንደምትደግፍ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ያለ ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ያለ ገደብ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እንዲቻል እንዲያደርጉ አሳስቧል።

በስድስት የኤርትራ መንግሥት ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የተጣለው ማዕቀብ ያተኮረው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ቀውስ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ ባላቸው ላይ እንጂ በኤርትራና በኢትዮጵያ ወይም በአጠቃላዩ የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ ላይ አይደለም ያለው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሌሎቹን የግጭቱ ተሳታፊዎችን ለምን እንዳላካተተ አስረድቷል።

አሁን በአሜሪካ ግምጃ ቤት በኩል የተጣለው ማዕቀብ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከህወሓት ጋር ተያያዥ የሆኑ አካላትን ያልነካው ጦርነቱን በውይይት ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤት ያመጡ እንደሆን ለማየት ጊዜ ለመስጠት በማሰብ ነው ብሏል።

ነገር ግን በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት ወገኖች ለሰላማዊ መፍትሄ የሚበጅ ትርጉም ያለው እርምጃ የማያሳዩ ከሆነ አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደምትጥል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አሳውቋል።