አሜሪካ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ በኤርትራው ጄነራል ላይ ዕቀባ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/TESFANEWS
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የኤርትራ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ላይ በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ማዕቀብ መጣሉን አስታወቀ።
ማዕቀቡ የተጣለባቸው የኤርትራው ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ፤ በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ በመሆን በተለያዩ ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚከሰሰው የኤርትራ ሠራዊት መሪ ወይም ከፍተኛ ባለሥልጣን በመሆናቸው እንደሆነ በአሜሪካ ግምጃ ቤት የውጪ ሐብቶች ቁጥጥር ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የኤርትራ መንግሥት አሜሪካ በአገሪቱ ላይ ያቀረበችውን ክስና በሠራዊቷ ኤታማዦር ሹም የወሰደችውን ይህንን እርምጃ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ተቀባይነት የሌለው ሲል አጣጥሎታል።
እንዲህ አይነቱ ከአሜሪካ አስተዳደር በኩል የሚሰነዘረው የስም ማጥፋት ዘመቻ አዲስ አይደለም ያለው የኤርትራ መንግሥት "የተሰነዘረበትን ፍጹም መሰረተ ቢስ ክስ አይቀበለውም" ብሏል።
ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኤርትራ ሠራዊት አዛዥ እንደመሆናቸው ጄነራል ፊሊጶስ በተፈጸሙት የተለያዩ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ማዕቀቡ እንደተጣለባቸው ተገልጿል።
በዚህም ምክንያት ግለሰቡ በአሜሪካ ውስጥ ባላቸው ንብረትና ገንዘብ ላይ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ላይ እገዳ የተጣለ ሲሆን ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣንም ሪፖርት እንደሚደረግ አመልክቷል።
ጄነራል ፊሊጶስ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ማግኒትስኪ ተብሎ በሚታወቀውና የሰብአዊ መብቶች ተጠያቂነትን ደንብ መሠረት በማድረግ በዓለም ዙሪያ ከባድ የመብት ጥሰት ፈጻሚዎችንና የሙስና ተሳታፊዎችን ተጠያቂ በሚያደርገው አሰራር አማካይነት ነው ተብሏል።
ኤርትራ ለአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ በሰጠችው ምላሽ ላይ እንዳለችው፤ እንዲህ አይነቱን ተጨባጭነት የሌላቸውን ተደጋጋሚ ክሶች በዝምታ አታልፈውም ያለው የኤርትራ መንግሥት "የአሜሪካ መንግሥት የሚሰነዝረው ሐሰተኛ ክስ ሊያረጋግጥለት የሚችል ሐቅ ካለው ገለልተኛ ለሆነ አካል እንዲያቀርብ" ጥሪ አቅርቧል።
ጨምሮም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ በአሜሪካ የሚፈጸመውን የዓለም አቀፍ ሕግጋት እንዲሁም የአገራትንና የሕዝቦችን ሉአላዊነት ጥስት ለማስተካከል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው "በኢትዮጵያ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተሳታፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል" ብሏል።
መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን አስታውሶ ነገር ግን ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊዎች ጦርነቱን ማባባሳቸውንና "ከኢትዮጵያ ወጥቶ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት ተመልሶ እንደገባ፣ ህወሓትም ጦርነቱን በማስፋፋት ወደ አጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች መግባቱን" ገልጿል።
ጨምሮም ኤርትራ በአስቸኳይና በዘላቂነት ኃይሎቿን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ እንዲሁም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉም ኃይሎች የተኩስ አቁም ድርድር እንዲጀምሩና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያቆሙ ጠይቋል።
በትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሪፖርቶቻቸው ሲያመለክቱ የቆዩ ሲሆን፤ ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ በግጭቱ ተሳታፊዎች ናቸው ባለቻቸው ኃይሎች ላይ ባለፈው ግንቦት ወር የጉዞ መዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለሥልጣናት፣ በወታደራዊና በደኅንነት አባላት እንዲሁም በአማራ ክልል ኃይሎችና በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ዕቀባ መጣሏን አስታውቃ ነበር።












