የጆ ባይደን ልዩ መልዕክተኛ ወደ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲና አረብ ኤምሬትስ ሊጓዙ ነው

ጄፍሪ ፌልትማን

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን

ከወራት በፊት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ጄፍሪ ፌልትማን ለሦስተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሦስት የአካባቢው አገራት እንደሚሄዱ ተነገረ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው ልዩ መልዕክተኛው ፌልትማን በአፍሪካ ቀንድ ወደ ኢትዮጵያና ጂቡቲ እንዲሁም ወደ ባሕረ ሰላጤው በማቅናት ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በዚህ ዙር ጉዟቸው ይጎበኛሉ።

ልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪ ፌልትማን ከመጪው እሁድ ነሐሴ 09/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ቀናት ወደ ሦስቱ አገራት በሚያደርጉት ጉዞ ከአገራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይገናኛሉ ተብሏል።

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ካጅ ሱሉቫን የልዩ መልዕክተኛው ጉዞ ይፋ ከመሆኑ በፊት በትዊተር ገጻቸው ላይ ፌልትማን "በዚህ ወሳኝ ወቅት" ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓዙ በፕሬዝዳንቱ መጠየቃቸውን ገልጸው ነበር።

ጨምረውም "ለወራት የተካሄደው ጦርነት በበለጠ ግጭት ሊሽር የማይችል ከፍ ያለ ስቃይንና መከፋፈልን በታላቋ አገር ላይ አስከትሏል" በማለት ሁሉም ወገኖች በአስቸኳይ ወደ ድርድር እንዲመጡ ጠይቀዋል ጃክ ሱሉቫን።

ይህ የባይደን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ትዊትም የልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪ ፌልትማን ዋነኛ የጉዞ አላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት ጉዳይ መሆኑን አመልክቷል።

ለወራት በትግራይ ክልል ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከወጣ በኋላ አሁን ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የትግራይ ክልሎች መስፋፋቱ ይታወቃል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የልዩ መልዕክተኛውን ጉዞ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው "ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም ለማስፈንና መረጋጋትን እንዲሁም ብልጽግናን ለመደገፍ ያሉ ዕድሎችን" በተመለከተ ውይይት ይደረጋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከተውን ጦርነት ተከትሎ ከወራት በፊት በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ጄፍሪ ፌልትማን ወደ አካባቢው አገራት የመጀመሪያውን ጉዟቸው ያደረጉት ከሚያዚያ 26 እስከ ግንቦት 5/2013 ዓ.ም ነበር።

በዚህም በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ስላለው ጦርነት እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሳቢያ በተፈጠረው አለመግባባት ዙሪያ ወደ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብጽ እና ሱዳን ተጉዘው ከአገራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

የልዩ መልዕክተኛው ሁለተኛው ዙር ጉዞ የነበረው ደግሞ ከግንቦት 23 አስከ 29/2013 ዓ.ም ድረስ የተደረገ ሲሆን በዚህ ጉብኝታቸው ፌልትማን ወደ ኳታርን፣ ሳዑዲ አረቢያን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ኬንያ ተጉዘው ከአገራቱ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።

ታዋቂው ዲፕሎማት ጄፍሪ ፌልትማን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕከተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ቀንድና የአካባቢው አገራት ይፋዊ ጉዞ ሲያደርጉ በመጪው እሁድ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን በዚህ ጉብኝታቸው በድጋሚ የሚያቀኑት ወደ ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ይሆናል።

በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ አሜሪካ መልዕክተኞችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ስትነጋገር የቆየች ሲሆን ከጄፍሪ ፌልትማን ቀደም ብሎ ሴናተር ክሪስ ኩንስ መንግሥታቸውን ወክለው ወደ ኢትዮጵያ መሄዳቸው ይታወሳል።

ከዚህ ባሻገር ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤይድ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ወደ ኢትዮጵያና ሱዳን ተጉዘው ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ለማግኘት ሳይችሉ መቅረታቸውን ገልጸው ነበር።

አሜሪካ በትግራይ ክልል የተከሰተው ጦርነት እንደሚያሳስባትና ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ችግሩን በድርድር እንዲፈቱ ከፕሬዝዳንቷ ጀምሮ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካይነት በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የሚደረገው ጥረት የተፈጠረውን ችግር ያላገናዘበና ወደ አንድ ወገን በማዘንበል ተገቢ ያልሆነ ጫና እየተደረገብኝ ነው ነው በማለት ቅሬታውን ሲገልጽ ቆይቷል።

line

ፌልትማን ማን ናቸው?

ጄፍሪ ፌልትማን በሹመታቸው ወቅት በተለይ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስላሉ ሁኔታዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አስታውቆ ነበር።

ፌልትማን በድርድርና የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ጥናትን በማካሄድና በአደራዳሪነትም ከፍ ያለ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።

ፌልትማን በፖለቲካዊና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞውንና የአሁኑን ዋና ጸሐፊዎች ባን ኪሙን እና አንቶኒዮ ጉቱሬዝን ያማከሩ ሲሆን፤ ለጸጥታው ምክር ቤት በሠላምና በደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ቆይታቸው ወቅትም በልዩ መልዕክተኝነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ፌልትማን በሊባኖስ፣ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በሃንጋሪና በሄይቲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።