በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት እንዲያበቃ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ዴ ክላርክ አረፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአፓርታይድ ሥርዓት ስር የመጨረሻው ነጭ የደቡብ አፍሪካ መሪ የነበሩት ኤፍ ደብሊው ዴ ክላርክ በ85 ዓመታቸው አረፉ።
ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ ባደረገችው ሽግግር ወቅት ቁልፍ ሚና የተጫወቱት ዴ ክላርክ ከወራት በፊት ካንሰር እንዳለባቸው በምርመራ ታውቆ እንደነበር ቃል አቀባያቸው ገልጿል።
ዴ ክላርክ ደቡብ አፍሪካን ከአውሮፓውያኑ መስከረም 1989 አስከ ግንቦት 1994 ድረስ መርተዋል።
የነጮች የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓትን ለማብቃት ዋነኛ የተባለውን እርምጃ በ1990 ላይ የፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴ ታጋዩን ኔልሰን ማንዴላን በመፍታት ወስደዋል።
ከዚያ በኋላም በ1994 በአገሪቱ የመጀመሪያው የብዝሃ ፓርቲዎች ምርጫ እንዲካሄድ አድርገዋል።
የቀድሞ ፕሬዝደንት ፋውንዴሽን ሐሙስ ዕለት ኤፍደብሊው ዴ ክላርክ ኬፕ ታዎን በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ማረፋቸውን አስታውቋል።
በደቡብ አፍሪካ ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ ለነበራቸው ተሳትፎ እአአ 1992 ላይ ከኔልሰን ማንዴላ ጋር በጋራ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ተቀብለው ነበር።








