ጦር መሳሪያ ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለፖሊስ እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, John Elk

የጦር መሣሪያ ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሁለት ቀናት ውስጥ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀረበ።

የከተማዋ የሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር) የአዲስ አበባን ሰላም ለማረጋገጥ የጦር መሣሪያ ያላቸው ግለሰቦች በአቅራቢያቸው ባለ ፖሊስ ጣቢያ በመገኘት እንዲያስመዘገቡ ጠየቁ።

ኃላፊው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ በሁለት ቀናት ውስጥ በማያሳውቁ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቃቸውን የመዲናዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ በቀጣይ ቀናት በከተማዋ በተለያዩ መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ቦታዎች ድንገተኛ ፍተሻ እንደሚደረግባቸው ገልጸው ለዚህም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ጥሪ የቀረበው የህወሓት አማጺያን የደቡብ ወሎ ከተሞች የሆኑትን ደሴ እና ኮምቦልቻን መቆጣጠራቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

የቀድሞ የመከላከያ ሚንስትር እና የአሁኑ የአዲስ አበባ የሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቀነአ ያደታ፤ የከተማዋ ወጣቶችም የመከላከያ ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን በተመለከተ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በሚያሰራጩ ላይ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቀዋል።

'በህወሓት ናፋቂዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይቀጥላል'

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የተቋቋመው የደህንነትና የፀጥታ ግብረ ኃይል "በህወሓት ደጋፊዎችና ናፋቂዎች ላይ እየተወሰደ ያለውን ሕጋዊ እርምጃ" ተጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል።

ግብረ ኃይሉ መኖሪያ ቤት ተከራይተው በጋራ የሚንቀሳቀሱ፣ ሰዋራ ስፍራ በመምረጥ ግንኙነት የሚያደርጉ የህወሓት "ደጋፊዎችና ናፋቂዎች" መኖራቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ፤ መኖሪያ ቤት፣ ንግድ ቤት፣ መጋዘን እና ተሽከርካሪ ያከራዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተከራዮችን ማንነት በጥንቃቄ በማጣራት መረጃውን በአስቸኳይ ለፖሊስ እንዲያሳውቁ አሳስቧል።

የክልሎች ጥሪ

የተለያዩ ክልሎች ከህወሓት አማጺያን ጋር በሚደረገው ጦርነት ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንሆናለን በማለት አስታወቁ።

የአፋር፣ የደቡብ ሕዝቦች፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ እና ሐረሪ ክልሎች ህወሓትን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን ካሉ የአገሪቱ ክልሎች መካከል ይገኙበታል።

ክልሎቹ ነዋሪዎቻቸው ህውሓትን ለመውጋት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ የህወሓት አማጺያንን ለማሸነፍ በሚደረገው ጦርነት የአፋር ክልል ህዝብ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል።

አማጺው ቡድን በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ለመግባት "ቢሞክርም አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ተባርሯል" ሲሉ አስተዳዳሪው አስታውሰዋል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤትም ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ ተከትሎ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል። ርዕሰ መስተዳደሩ ደስታ ዴላሞ የክልሉ ህዝብ ዛሬ ነገ ሳይል ሁለንተናዊ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ወደ ግንባር መዝመት፤ አካባቢን ከሰርጎ ገቦች መጠበቅ እና ለሠራዊቱ የሚደረጉ የሞራል እና የአይነት ድጋፎችን ማጠናከር የገጠመንን የህልውና አደጋ በድል ለመወጣት ዋናው ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ እና ፈጣን የሆነ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቃልም ብለዋል።

በተመሳሳይ የሐረሪ ክልል፣ የክልሉ ህዝብ የሚችለው ወደ ግንባር በመዝመት፤ የማይችለው ገንዘብ በማዋጣት፣ ስንቅ በማዘጋጀት እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስቧል።

የደቡብ ክልል ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልም የክልሉ ወጣቶች የመከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉና ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ፀጥታ እንዲጠብቁ ጠይቋል።

የሶማሌ ክልል ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ኡመር በበኩላቸው በህወሓት ጋር በሚደረገው ጥረት የሶማሌ ህዝብና መንግሥት ምንጊዜም ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነው ብለዋል።