የኮሮናቫይረስ መነሻ ሳይታወቅ ሊቀር እንደሚችል የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ተናገሩ

የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት የኮሮናቫይረስ መነሻ በትክክል ሳይታወቅ ሊቀር እንደሚችል ይፋ አደረጉ።

ስለ ወረርሽኙ መነሻ ምርመራ ሲያደርጉ የነበሩ ተቋማቱ እንዳሉት፤ የቫይረሱን መነሻ ማወቅ ባይቻልም ቫይረሱ ሰዎችን ለመጉዳት በመሣሪያነት እንዲውል እንዳልተሠራ ደርሰውበታል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው የተላለፈ ወይም ከቤተ ሙከራ ሾልኮ ያመለጠ ሊሆን የሚችልበት እድል አለ።

ከሁለቱ መላ ምቶች ባለፈ ስለ ቫይረሱ መነሻ ጠንካራ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችል መረጃ እንደሌለ ተገልጿል።

ይህ የደኅንነት ተቋማቱ መረጃ ይፋ ከሆነ በኋላ ቻይና ሪፖርቱን ተችታለች።

ጆ ባይደን ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ በመጀሪያዎቹ 90 ቀናት ውስጥ የተደረገው ምርመራ ባለፈው ነሐሴ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። አሁን የወጣው ሪፖርት የነሐሴው ተከታይ ነው።

ከዚህ በፊት በወጣው ሪፖርት ላይ የደኅንነት ባለሙያዎች ስለ ኮሮናቫይረስ አነሳስ የተለያየ አቋም እንዳላቸው አስታውቆ ነበር።

አራት የደኅንነት ተቋማት ቫይረሱ የተነሳው ከእንስሳት እንደሆነ "በመጠኑ እንደሚገምቱ" ሲናገሩ፤ አንድ የደኅንት ተቋም ግን በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያ ሰው ቫይረሱን ያገኘው ከቤተ ሙከራ እንደሆን "እርግጠኛ መሆኑን" ገልጿል።

በቻይናዋ ዉሃን ከተማ በሚገኘው የቫይረስ ጥናት ተቋም ባለ ቤተ ሙከራ ውስጥ ምርምር እየተደረገ ሳለ በድንገት ለቫይረሱ የተጋለጠ ሰው እንደሚኖር መላ ምት ተቀምጧል።

ኮሮናቫይረስ ዉሃን ውስጥ እስኪሰራጭ ድረስ የቻይና መንግሥት በቫይረሱ የተያዘ ሰው እንዳለ እንዳላወቀ ተጠቁሟል።

ሆኖም ግን ቻይና ዓለም አቀፍ ምርመራውን ለማሰናከል በሚል መረጃ ደብቃለች ተብላ ተወንጅላለች።

ቫይረሱ መጀመሪያ ላይ የተነሳው ከዓሣ ገበያ እንደሆነ የቻይና መንግሥት መናገሩ አይዘነጋም። ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰዎች የተላለፈ ነው የሚለው መላ ምት የመጣውም ይህንን ተከትሎ ነው።

የአሜሪካ ተመራማሪዎች በበኩላቸው ቫይረሱ በድንገት ከቤተ ሙከራ ሾልከ የወጣ ነው ወደሚለው መላ ምት ያዘነብላሉ።

ቻይና በበኩሏ ከቤተ ሙከራ ያመለጠ ቫይረስ ነው የሚለውን አትቀበልም።

በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ ምርመራውን ተከትሎ "አሜሪካ የቫይረሱን መነሻ ለማወቅ ከሳይንቲስቶች ይልቅ የደኅንነት ሠራተኞች አሰማርታለች። ይህ የሚያሳየን ምርመራው ፖለቲካዊ መሆኑን ነው" ሲል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ምላሽ ሰጥቷል።

ቻይና የቫይረሱን መነሻ ለማግኘት የሚደረገውን ምርምር "ፖለቲካዊ" ለማድረግ መሞከሩን ብትቃወምም፤ ለሳይንስ መር ምርምር በሯ ክፍት እንደሆነ አስታውቃለች።

አስካሁን በመላው ዓለም ወደ 240 ሚሊዮን ሰዎች ገደማ በኮቪድ-19 ተይዘዋል። ከ4.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተዋል።