የቱርኩ ፕሬዘዳንት ኤርዶዋን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን እንኳን ደስ አለዎት አሉ

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ማስተላለፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በማኅበራዊ ገጾቹ ያወጣው ጽሑፍ እንደሚለው፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በአገር መሪነት በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ኤርዶዋን አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም የጠቅላይ ሚንስትሩ የሥልጣን ዘመን "ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ ብልፅግና የሚያመጣ" እንዲሆን መመኘታቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ከተሰማሩ እና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካፈሰሱ መካከል የቱርክ ዜጎች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም የሰሜኑ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ ስማቸው በተደጋጋገሚ ከሚነሳ አገሮች መካከል ቱርክ ትገኝበታለች።

ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የአመራር ዘመን የቱርክ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ይጎለብታል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አትቷል።

"እስካሁን የዘለቀው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ወዳጅነት እና ትብብር ከዚህ በኋላም እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለኝ" ማለታቸውንም አስታውቋል።

በ2013 ዓ. ም. ነሐሴ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ቱርክ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል። በምጣኔ ሀብት እና በሌሎችም ዘርፎች ሁለቱ አገራት ለመደጋገፍ ስምምነት መፈራረማቸውም አይዘነጋም።

በወቅቱ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ከመጠየቃቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል አሸማጋይ ለመሆን እንደሚሹም ተናግረው ነበር።

ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ቱርክ ያደረጉትን ጉዞ "የተሳካ" ሲሉ ኤርዶዋን እንደገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መረጃ ይጠቁማል።

በተጨማሪም የጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኝት "በሁለቱ አገሮች መካከል የዘለቀውን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር 125ኛ ዓመት ክብረ በዓል ያደመቀ" ሲሉ ገልጸውታል ተብሏል።