ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፒካሶ የሥዕል ሥራዎች ከ20 ዓመት በኋላ በ110 ሚሊዮን ዶላር ተሸጡ
አስራ አንድ የፓብሎ ፒካሶ የጥበብ ሥራዎች ላስ ቬጋስ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ከተሰቀሉ ከ20 ዓመታት በኋላ 110 ሚሊዮን ዶላር ገደማ አውጥተው ተሸጡ።
ኤምጂኤም ሪዞርትስ የተባለው ኩባንያ ንብረት የሆኑትእነዚህ የጥበብ ሥራዎች ቤላጂዮ በተሰኘው ሆቴል ፒካሶ ሬስቶራንት ውስጥ ነበር ተሰቅለው የቆዩት።
የፒካሶን ሥራዎች በጨረታ በ110 ሚሊዮን ዶላር የሸጠው ኩባንያ በገንዘቡ ሌሎች የጥበብ ሥራዎችን እንደሚገዛ አስታውቋል።
ድርጅቱ ዘጠኝ የፒካሶ ሥዕሎችንና ሁለት የሴራሚክ ሥራዎችን ለጨረታ አቅርቦ ነው ለገዢዎች የሸጠው።
እነዚህ በፈረንጆቹ 1973 የሞተው ስፔናዊው አርቲስት የፒካሶ ሥራዎች ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ናቸው ተብሏል።
40 ሚሊዮን ዶላር ያወጣው ሥዕል የፒካሶ ፍቅረኛ የነበረችው ሜሪ ቴሬሳ ዋልተር ደማቅ ቀይ ብርቱካናማ ኮፍያ አጥልቃ የምትታይበት ነው።
ይህ ሥዕል መጀመሪያ የተገመተው ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
ሌላኛው ዘመን አይሽሬ የጥበብ ሥራ 'ማን ኤንድ ቻይልድ' የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው የሸራ ቅብ ሲሆን 24.4 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል።
ሁለት ሜትር ቁመት ያለው ይህ የጥበብ ውጤት በፈረንጆቹ 1959 ፒካሶ የስኬት ጣራ ላይ ሳለ የሠራው ነው ተብሏል።
16.6 ሚሊዮን ዶላር ያወጣው ሌላኛው የፒካሶ ሥራ ደግሞ ፓሪስ በናዚ እጅ ሥር ሳለች የተሳለው ሥራ ነው።
የቤላጂዮ ሆቴል የቀድሞ ባለቤት የነበረው አሜሪካዊው ጉምቱ ባለሃብት ስቲቭ ዊን ነው የፒካሶን ሥራዎች ከ20 ዓመታት በፊት መሰብሰብ የጀመረው።
ሰውዬው የዌን ሪዞርትስ ኃላፊ የነበረ ሲሆን በቀረበበት የፆታዊ ትንኮሳ ክስ ምክንያት ሥራውን ለቋል።
ስፔናዊው ሰዓሊ ፓብሎ ፒካሶ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ አርቲስት ነበር ይባልለታል። በ92 ዓመቱ የሞተው ፓብሎ በሙያ ዘመኑ እጅግ በርካታ የአሳሳል ዘይቤዎችንና ጭብጦችን ዳስሷል።
ፒካሶ ትውልዱ ስፔን ይሁን እንጂ አብዛኛውን ህይወቱን ያሳለፈው ፈረንሳይ ውስጥ ነበር።