ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፍሪካ ጥንታዊና ዘመናዊ ድንቅ ሥነ ሕንጻ ጥበብ ውጤቶች
የግብፅ ፒራሚዶች በመላው ዓለም በስፋት የሚታወቁ ቢሆንም በርካታ በጥበብ የተሞሉ ብዙ ያልተባለላቸው የአፍሪካ ሥነ ሕንጻዎች አሉ።
የሥነ-ሕንጻ ጥበብ ባለሙያዎቹ አዲል ዳላባይ እና ሊቪንግስተን ሙካስ ድንቅ የአፍሪካ ሥነ ሕንጻ ውጤቶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ተነስተዋል።
ሁለቱ የሥነ ሕንጻ ባለሙያዎች በቅርቡ ከሰሃራ በታች ስለሚገኙ ሥነ ሕንጻዎች የሚያወሳ መጽሐፍ ያሳተመ ቡድን አባላት ናቸው።
በዚህ መጽሐፍ ላይ ከጥንታዊ ሕንጻዎች እስከ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ሕንጻዎችን ተቃኝተውበታል።
ከዚህ በታች ስምነቱን ታሪካዊ እና ተምሳሌታዊ ሕንጻዎች ቀርበዋል።
1) የፋሲለደስ ቤተ-መንግሥት- ኢትዮጵያ 17ኛው ክፍለ ዘመን
ይህ ቤተ-መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ጎንደር ከተማ ፋሲል ግቢ ውስጥ ይገኛል።
በዚህ ስፍራ ወደ 20 የሚጠጉ ሕንጻዎች ይገኛሉ። እነዚህ ሕንጻዎች እንደ የንጉሣውያን መኖሪያ እና ማረፊያ፣ ቤተ-ክርስቲያናት፣ ገዳማት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ግንባታዎችን አካተዋል።
የዚህ ሕንጻ ቅርጽ ጽንሰ ሃሳብ ወደ አካባቢው ከመጡ ሚሲኦኖች ተጽእኖ የመጣ እንደሆነ ይታመናል።
2) ልደታ ገበያ፤ ኢትዮጵያ - 2012
ዘመናዊ ገጽታ ያለው ይህ ሕንጻ የሚገኘው በመሃል አዲስ አበባ ልደታ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነው።
ሕንጻው ክፍተት እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራው ተፈጥሯዊ ብርሃን በቀላሉ ዘልቆ እንዲገባ እና አየር እንዲዘዋወር ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ነጸብራቃው ነጩ ሕንጻ የኢትዮጵያ ባህላዊ ጨርቅ ያመላክታል።
3) ካሱቢ ቶምበስ (የመቃብር ስፍራ) ኡጋንዳ - እአአ 1882
በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ የሚገኘው እና በርካታ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ካሱቢ የቡጋንዳ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት መቀበሪያ ቦታ ነበር።
ሕንጻው የተገነባው አብዛኛው ከእንጨት ሲሆን የሕንጻው የውስጥ ክፍልን ልዩ ስፍራ ከሚሰጠው ደን ጋር ለማመሳሰል እና 52ቱን የቡጋንዳ ጎሳዎች ለመወከል በክብ ቀርጽ በ52 ምሶሶዎች ቆሟል።
ትውልዱ በኡጋንዳ የሆነው ሙካሳ ይህን የመቃብር ስፍራ የጎበኘው ገና የ10 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። "ዘመናዊ የግንባታ መሳሪያዎች በሌሉበት ባህላዊ የግንባታ ዘዴዎችን በመጠቀም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነበር የተገነባው። . . . አስደናቂ ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
4) ሂክማ ኮምፕሌክስ- ኒጄር እአአ 2018
ይህን ሕንጻ የቀድሞ የሃውሳ መስጅድ ወደነበረበት ለመመለስ የተገነባ ሕንጻ ነው። በውስጡ ማሕበራዊ አገልግሎቶች ሊከወኑ የሚችሉበት ቦታ እና ቤተ-መጽሐፍት አለው።
የሥነ ሕንጻ ባለሙያው ዳላባይ ይህን ሕንጻ አስደናቂ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ ሕንጻው ጥንታዊ እና ዘመናዊ እንከን የለሽ ጥምረት ነው።
"ይህን ዘመናዊ ሕንጻ በኒጀራያውያን ባህል ውስጥ ስር የሰደደ ስለመሆኑ ግልጽ ነው" ይላሉ ጀርመናዊው የሥነ ሕንጻ ባለሙያ።
5) ማሮፔንግ የጎብኚዎች ማዕከል- ደቡብ አፍሪካ - 2006
የሰው ልጅ መገኛ የዓለም የቅርስ ቦታ ተብሎ የሚታወቀው ማሮፔንግ፤ ጎብኚዎች የሰው ልጅ እድገት ምን እንደሚመስል እንዲማሩ ይረዳል።
ይህ አስደናቂ ሕንጻ የተገነባው በደቡብ አፍሪካው ጂኤፒፒ የሥነ ሕንጻ ባለሙያዎች እና ኤምኤምኤ ስቱዲዮ ነው።
ግንባታው ከመሬት በላይ ከፍ ብሎ የተሰራ እና ከተፈጥሮ ጋር በትክክል የተዋህደ የመቃብር ቦታ ይመስላል።
6) የሜሮዌይ ፒራሚዶች- ከክርስቶስ ልደት በፊት 300
እነዚህ ጥንታዊ ግንባታዎች የሚገኙት ከሱዳን መዲና ካርቱም በ125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በናይል ሸለቆ ውስጥ ነው።
ይህ በተባበሩት መንግሥታት የየትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው ቦታ የጥንታዊ ኩሽ ስርወ መንግሥት መቀመጫ ነበር። በአከባቢው ቁፋሮዎች ተካሂደው የቤተ-መንግሥት ፍርስራሶች ተገኝቷል።
የዚህ መቃብር ስፍራ ፒራሚዶች የተገነቡት ከአሸዋ እና ከድንጋይ በተሰሩ ብሎኬቶች ነው።
7) ባሶቶ ቤቶች፣ሌሴቶች - የተገነባበት ጊዜ አይታወቅም
ይህ ጥንታዊ ግንባታ በተለያዩ የአካባቢውን ባህል በሚገልጹ ቀለማት ያሸበረቀ ነው። ቀይ ቀለም ውልደት እና መስዋትነትን፣ ነጭ ቀለም ንጽህናን እና ሰላምን፣ ጥቁር ቀለም የቀደመውን ትውልድ የሚወክል ሲሆን "ጥቁር ዝናባማ ደመና" በዝናብ ይመሰላል።
ሙካሳ የባሶቶ ቤቶች ሁልጊዜም ከመሬት አቀማመጡ ጋር በተያያዘ ያስደንቁኛል ይላል። የቀለም አጠቃቀም እና ቅርጻቸው አስደናቂ ነው በማለት ይናገራል።
8) ታላቁ መስጅድ- ቤኒን እአአ 1912-1935
ይህ በቤኒን መዲና ፖርት-ኖቮ የሚገኘው መስጅድ የአፍሮ-ብራዚል ሥነ ሕንጻ ማሳያ ጥሩ ምሳሌ ነው። በብራዚል በ17ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ከዚህ ሕንጻ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ በርካታ አብያተክርስቲያናት ተገንብተዋል።
ቢጫ፣ ቡኒ፣ አረንጓዴ እና ሰሚያዊ ደማቅ ቀለማት ከብራዚል ጥንታዊ የሥነ ሕንጻ ግንባታ ጥበብ ጋር ቁርኝት አላቸው።