ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእስራኤል 1 ሺህ 500 አመታትን ያስቆጠረ የወይን መጥመቂያ ስፍራ ተገኘ
በወቅቱ የዓለማችን ትልቁ ነበር የተባለ 1 ሺህ 500 ዓመታትን ያስቆጠረ የወይን መጥመቂያ ስፍራ በእስራኤል ውስጥ መገኘቱን የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
ከቴልአቪቭ በስተደቡብ ያቢን ከተማ በሚገኝ ስፍራ ተቆፍሮ የተገኘው የወይን መጥመቂያ በባይዛንታይን ዘመን የተቆረቆረ እንደሆነ ተነግሯል።
ይህም መጥመቂያ በአመት ሁለት ሚሊዮን ሊትር ወይን ያመርታል የሚል ግምትም ባለሙያዎቹ አስቀምጠዋል።
የመጥመቂያ ስፍራው የተራቀቀ የማምረት ሂደትን ይከተል የነበረ ሲሆን ሜድትራንያን አካባቢ ባሉ ስፍራዎችም ይላክ ነበር።
በቦታው የሚሰሩ ሰዎች በመጥመቂያው ትልቅነት እንደተገረሙ ተናግረዋል።
የጥበቃ ስፍራው ከተጠናቀቀ በኋላም ይህንን ውስብስብ የወይን መጥመቂያ ለጎብኝዎች መስህብ ለማድረግ ዕቅዶች እንዳሉም ተገልጿል።
ጣቢያው አምስት የመጭመቂያ ስፍራዎችን የያዘ ሲሆን፣ በተጨማሪም የወይኑ ጣዕም ለማስተካከል ይቻል ዘንድ ለአመታት ማስቀመጥ የሚቻልበት ማከማቻ ስፍራ፣ ማሸጊያ መጋዘኖች፣ ያገለገሉ ማሰሮዎችን ማቃጠያ ትልቅ ቦታም የያዘ ነው።
ወደ አውሮፓ፣ ወደ ሰሜን አፍሪካ እና እስያ ከተላከ በኋላም ጋዛ እና አሽኬሎን የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር።
በመላው የሜዲትራንያንን ቀጠናም ውስጥ ከፍተኛ የዝና ማማ ላይ ደርሶ የነበረው ይህ ወይን በጥራቱ ይደነቅ ነበር።
በወቅቱ ወይን ከውሃ በላይ መሰረታዊ መጠጥ ተደርጎ የሚቆጠርበትም ወቅት ነበር።
"ወይን ዋነኛው፣ መሰረታዊና አስተማማኝ መጠጥ ነበር ለዚህም ምክንያቱ ውሃው አብዛኛውን ጊዜ ይበከል ስለነበር ነው" በማለት ከመሬት ቁፋሮው ዳይሬክተሮች አንዱ የሆነው ጆን ሴሊግማን ተናግረዋል።