ታይዋን ለቻይና እንደማትንበረከክ መሪዋ ተናገሩ

ፕሬዚዳንት ፃይ ኢንግ ዊን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በታይዋን ላይ ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት በአሁኑ ወቅት ፕሬዚዳንት ፃይ ኢንግ ዊን አገራቸው ለቻይና ጫና እንደማንትንበረከክና ባላት ዴሞክራሲያዊ የፅንሰ ሃሳብ መርሆች እየተዳደረች ትቀጥላለች በማለት ተናግረዋል።

መሪዋ አክለውም "ስኬታችን በጨመረ ቁጥር ከቻይና የሚደርስብን ጫናም የከፋ ይሆናል" ብለዋል።

በታይዋን ብሄራዊ ክብረ በዓል ንግግር ያደረጉት የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በበኩላቸው "ውህደቱን ለማጠናቀቅ" ቃል ገብተዋል።

ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ብትቆጥርም በቻይና በኩል ተመሳሳይ አረዳድ የለም በተፃራሪው ከቻይና እንደተገነጠለች ግዛት ነው የምትመለከተው።

ቻይና የምትለውንም ውህደት ለማሳካት ኃይል ልትጠቀም ትችላለች።

ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆነው ቻይና ከቅርብ ወናት ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር ጄት ወደ ታይዋን የአየር መከላከያ ቀጠና መላኳ ነው።አንዳንድ ተንታኞች በረራዎቹ ለታይዋን ፕሬዝዳንት እንደ ማስጠንቀቂያ ሊታዩ ይችላሉ ብለዋል።

ፕሬዚዳንቷ በበኩላቸው "ታይዋን ለዴሞክራሲ በመወገን ቆማለች" በማለት ተናግረዋል።

ደሴቲቷ ነፃነት፣ ዴሞክራሲ ወይም ሉዓላዊነትን በነፈገ መልኩ "ቻይና የዘረጋችልንን መስመር" እንድትወስድ ማስገደድ እንደማይቻል አስረድተዋል።

የቻይና ወታደራዊ በረራዎች ወደ ታይዋን የአየር መከላከያ ቀጠና መስመር አልፈው መግባታቸው በብሔራዊ እና በአቪዬሽን ደህንነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ " ሁኔታው በባለፉት 72 ዓመታት በነበረው ወቅት የበለጠ የተወሳሰበ እና የማይገመት ነበር" ብለዋል።

ታይዋን "በችኮላ እርምጃ አትወስድም" ቢሉም ነገር ግን መከላከያዋን ታጠናክራለች ብለዋል።

መሪዋ ከቻይና አመራሮች ጋር በእኩል ደረጃ ለመወያየት ያቀረቡትን ሃሳብ በድጋሜ ቢያነሱም "ተገንጣይ" የሚል ስያሜ የሰጧቸው የቻይና አመራሮች ውድቅ አድርገውታል።

ፕሬዚዳንቷ እንደገና በባለፈው ዓመት ሲመረጡ በከፍተኛ ድምፅ ሲሆን ቻይናን ለመገደደር ቃል ገብተዋል። ፕሬዚዳንቷ ንግግር ካደረጉ በኋላም የታይዋን ተዋጊ አውሮፕላኖች ሲያንዣብቡ ታይተዋል።

ስለ ቻይና እና ታይዋን ጥቂት መሰረታዊ ነገሮች

ቻይና እና ታይዋን ለምን ደካማ ግንኙነት ኖራቸው? በአውሮፓውያኑ 1940 ዎቹ ቻይና እና ታይዋን በእርስ በእርስ ጦርነት ተከፋፈሉ። ነገር ግን ቻይና አሁንም ቢሆን ደሴቲቷ አስፈላጊ ከሆነ በኃይልም ቢሆን ትመለሳለች የሚል እምነት አላት።

ታይዋን የምትተዳደረው እንዴት ነው? ደሴቲቱ የራሷ ሕገ መንግሥት ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች ፣ እና በጦሩ 300 ሺህ ገደማ የሚሆኑ የሰራዊት አባላት አሏት።

•እንደ ሃገር ለታይዋን ማን እውቅና ሰጣት? ለታይዋን ዕውቅና የሰጧት ጥቂት አገሮች ብቻ ናቸው። በርካታዎቹ ቤጂንግን መቀመጫ ላደረገው የቻይና መንግሥት እውቅና ይሰጣሉ። አሜሪካ ከታይዋን ጋር ኦፊሴላዊ ግንኙነት የላትም ነገር ግን ደሴቲቱ እራሷን ለመከላከል የሚያስችል ድጋፍ እንድትሰጥ የሚጠይቅ ሕግ አላት።