ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ልጆቻቸው ታዋቂ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ጉቦ የሰጡ ወላጆች የ20 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል ተባለ
በአሜሪካ ሁለት ሀብታም አባቶች ልጆቻቸው በታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲገቡ ጉቦ በመስጠታቸው በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተባሉ።
ጉዳዩን የተመለከቱት በአሜሪካዋ ቦስተን የሚገኙ ዳኛ በሰጡት ብይን በተለያዩ ዘርፎች ከፍተኛ ሀብት ያላቸው ጋማል አዚዝ እና ጆን ዊልሰን የተባሉት ግለሰቦች በማጭበርበርና ጉቦ በመስጠት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።
ግለሰቦቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ የሚሰጠው በመጪው የካቲት ወር ላይ ሲሆን እያንዳንዳቸው አስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድባቸው ይችላል።
የአሜሪካ ፌደራል ዐቃቤ ሕግ አንደኛውን ተከሳሽ ጋማል አዚዝ ከአራት ዓመት በፊት ሴት ልጁ ሳውዘርን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ እንድትጋባ ለማድረግ 300 ሺህ ዶላር ከፍሏል የሚል ክስ ነው ያቀረበበት።
በተጨማሪም ልጁ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቷ ውስጥ ለሚገኝ የቅርጫት ኳስ ቡድን ለመጫወት ሳትችል የቀረች ብትሆንም ኮከብ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች እንደሆነች ተደርጋ ቀርባ ነበር።
ጆን ዊልሰንም ልጁ በሐሰት ስፖርተኛ መሆኑ ተገልጾ ከመቅረቡ በተጨማሪ 220 ሺህ ዶላር ጉቦ ከፍሎ ወደ ዩኒቨርስቲው እንዲገባ ተደርጓል የሚል ክስ ቀርቦበታልል። ነገር ግን ልጁ በስፖርቱ ውስጥ ተሳትፎ የሌለውና ለመመረጥም ብቁ እንዳልነበረ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጆን ሁለት ሴት ልጆቹ ስታንፈርድ እና ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲዎች እንዲገቡ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ ለመክፈት ሞክሯልም ተብሏል።
ሁለቱም ባለሃብቶች የዚህ ሁሉ ጉቦ ቅሌት አስተባባሪ እንደሆነ በባለሥልጣንት በሚነገርለት ዊሊያም ሲንገር በተባለ ግለሰብ መታለላቸውን በመግለጽ ተከራክረዋል። ለግለሰቡ የከፈሉት ገንዘብ ለጉቦ እንደሚውል እንደማያውቁም ገልጸው ነበር።
ሲንገር የተባለው ግለሰብ በቀረበው ክስ ውስጥ ከባለሥልጣናት ጋር በመተባበሩ አስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረበም።
ግለሰቡ ለሁለቱ አባቶች ዩኒቨርስቲዎቹ ለስፖርተኛ ተማሪዎች ያላቸውን ክፍት ቦታዎች በመጠቀም ልጆቻቸውን "በኋላ በር" በታዋቂዎቹ ዩኒቨርስቲዎች የመማር ዕድል እንደሚያስገኝላቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር።
ሁለቱ አባቶች አዚዝ እና ዊልሰን በዳኛው በተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ ጥፋት ከ50 በላይ የሚሆኑ ወላጆች፣ የስፖርት አሰልጣኖች እና የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በአገር ደረጃ እየታየ እንደሚገኝ ተነግሯል።
በዚህ ክስ በርካታ ታዋቂ ሰዎች ስማቸው የተነሳ ሲሆን አንዳንዶቹ የፈጸሙትን ጥፋት አምነው ይቅርታ በመጠየቃቸው ክስ ሳይመሰረትባቸው ቀርቷል።