ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እንግሊዛዊው 35 ኪሎግራም የሚመዝኑ ኩላሊቶቹ በቀዶ ህክምና ተወገዱለት
በአንግሊዝ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ሁለቱም ኩላሊቶች በከፍተኛ ደረጃ ትልቅ መሆናቸውን ተከትሎ እንዲወጡለት መደረጉን ሐኪሞች ተናገሩ።
የ 54 ዓመቱ ዋረን ሂግስ በአጠቃላይ 35 ኪሎ ግራም የሚመዝኑትን የአካል ክፍሎቹን ለማስወገድ የሁለት ሰዓት ቀዶ ጥገና አድርጓል።
ግለሰቡ ኩላሊቶቹ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ትልቅ ከመሆናቸው የተነሳ ክብረ ወሰንም ይዟል ተብሏል
የአንድ ወድ ልጅ አባት የሆነው እና ፖሊሲስቲክ የተባለ የኩላሊት በሽታ ያለበት ግለሰቡ "በየትኛውም መንገድ ቢለካ" ትልቅ ኩላሊት ያለው በመሆን ክብረ ወሰን እንደሚሰብር ሐኪሞቹ እንደነገሩት አስታውቋል።
በሆዱ መጠን ላይ ያለውን ልዩነት "አስገራሚ ነው" ብሏል።
ከእንግሊዟ ዊንድሶር የመጣው ሂግስ ትልቁ የቀኝ ኩላሊቱ 15 ኪሎ ሲመዝን ተጨማሪ 5 ኪሎ የሚመዝን ፈሳሽም በላዩ ላይ ነበር ብሏል።
ቀደም ሲል በዓለም ላይ ትልቅ የነበረው ኩላሊት በሕንድ በቀዶ ጥገና የተወገደው እና 7.4 ኪ.ግ የሚመዝነው እንደሆነ ይታመን ነበር።
"የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ሁሉንም አረጋግጦ ነበር። እናም አዎ በእያንዳንዱ መለኪያ ክብረ ወሰኑን አሻሽለነዋል።" ብሏል።
"ርዝመቱ በሚለካበት ጊዜ፣ ከያዘው ፈሳሽ ጋር ሲመዘን እና ፈሳሹ ከተወገደ በኋላም አሻሽዬዋለሁ።" ያለው ግለሰቡ ሆኖም "ይህ የምኮራበት ነገር አይደለም።" ይላል
ፒኬዲ በኩላሊት ውስጥ ሲስቲክ የሚባሉ ትናንሽ ፈሳሽ የተሞሉ ከረጢቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋል።
ከአምስት ዓመት በፊት በውርስ የሚመጣው ህመም ኩላሊቶቹ ከሚገባው በላይ አምስት እጥፍ እንዲያድጉ አድርጓቸዋል ሲሉ ዶክተሮቹ ተናግረዋል።
ኩላሊቶቹ ሳንባውን፣ ሆዱን እና ልቡን መጉዳት ስለጀመሩ "ሕይወት አድን" ቀዶ ጥገና መደረጉ አስፈላጊ መሆኑ እንደተነገረው ሂግስ አስታውቋል።
በተጨማሪ ትልቅ የሆድ እብጠት እንዲኖረው ምክንያት ሲሆን እብጠቱ ከሐምሌው ቀዶ ጥገና በኋላ "አስደናቂ" ለውጥ አምጥቷል ብሏል።
ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት ወደ ጂምናዚየም የተመለሰ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመትም በኤሌክትሪክ ብስክሌት ትሪያትሎን (ሩጫ፣ ዋና እና ሳይክልን ያካተት ውድድር) ላይ ለመወዳደር በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
የቀድሞው የሂሳብ ባለሙያው በየሁለት ቀኑ የዲያሊሲስ ማድረጉ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰበት መሆኑን ጠቅሷል።
"በዲያሊሲስ ማለፍ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መግለጽ አልችልም" ብሏል።
በሚቀጥለው ዓመት ለኩላሊት ንቅለ ተከላ ብቁ ለመሆን በመዝገቡ ውስጥ እንደሚገባ ተስፋ ያደርጋል።