የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ይወያያል ተባለ

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ [ከሌላ ስብሰባ ላይ የተወሰደ]

የፎቶው ባለመብት, EVAN SCHNEIDER

የምስሉ መግለጫ, የጸጥታው ምክር ቤት አባላት በስብሰባ ላይ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አርብ መስከረም 20/2014 በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ እንደሚወያይ ተገለጸ።

የምክር ቤቱ መርሃ ግብር እንዳመለከተው ቀደም ሲል ከተያዘ ጉዳይ ውጪ በሆነ መድረክ የፀጥታው ምክር ቤት አባልት በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ ይወያያሉ ብሏል።

ይህ የምክር ቤቱ ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደገቡ በመግለጽ ከግዛቱ እንዲወጡ ካዘዘ በኋላ የሚደረግ ስብሰባ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔን ተከትሎ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በእርምጃው መደንገጣቸውን አመልክተው፤ ውሳኔውን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣንት ጋር እየተወያዩ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን መንግሥታት በዓለም አቀፉ ድርጀት የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን እንዲያጤን ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው የተመድን ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን የተቃውሞ ኃሳብ ደግፈው ድምፃቸውን እንደሚያሰሙ በትዊተር ገጻቸው አጋርተዋል።

"በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍተኛ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ቅጽበት ሰባት የተባበሩት መንግስታት ሠራተኞችን ከኢትዮጵያ ማስወጣት ተቀባይነት የለውም። ሕይወትን ማዳን እና የተቸገሩትን መርዳት የኢትዮጵያ መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት ነው። " በማለትም አስፍረዋል።

ዛሬ ይካሄዳል የተባለውን ይህንን የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እንዲካሄድ የጠየቁት የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ኢስቶኒያ ፣ ፈረንሳይ፣ አየርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ዩክሬንና አሜሪካ ናቸው።

አስራ አምስት አባላት ያሉት ከፍተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውሳኔ አካል የሆነውን የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤትን የፕሬዝዳንትነት መንበር ዛሬ በሚጀምረው የፈረንጆቹ የጥቅምት ወር የምትረከበው ኬንያ ናት።

ምክር ቤቱ ለዛሬ በያዘው ስብሰባው በጥቅሉ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ እንደሚወያይ የተነገረ ሲሆን፤ ሐሙስ ዕለት የኢትዮጵያ መንግሥት የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞችን ከአገሩ እንዲወጡ የሰጠው ውሳኔ ላይ እንደሚነጋገር ይጠበቃል።

በተጨማሪም በሠሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ የትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትንና ያለውን አሳሳቢ ሰብአዊ ቀውስ በተመለከተ ሊወያይ ይችላል ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የትግራይ ክልል ይፋዊ ባልሆነ የሰብአዊ እርዳታ እገዳ ስር ነው ሲል የገለጸ ሲሆን፣ የድርጅቱ የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በክልሉ ረሃብ ሳይከሰት እንደማይቀርም ብለው እንደሚገምቱ መግለጻቸው ይታዋሰል።

ኃላፊው የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦት የያዙ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ እንዲያደርግ ጠይቀው "ይህ ችግር ሰው ሰራሽ ነው፣ መንግሥት እርምጃ ከወሰደ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል" ሲሊ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

ኒው ዮርክ ሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተልዕኮ በበኩሉ ወደ ትግራይ እርዳታ እንዳይገባ "እገዳ ተጥሏል የሚባለው ክስ መሰረተ ቢስ ነው" ሲል አጣጥሎታል።

ጨምሮም የረድኤት ድርጅቶች "እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችሉ የጭነት ተሽከርካሪዎች እጥረት የገጠማቸው ቀደም ሲል ወደ ትግራይ እርዳታ ለማድረስ የተሰማሩ መኪኖች ሳይመለሱ በመቅረታቸው ነው" ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

በትግራይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የእርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የመንግሥታቱ ድርጅት ሲገልጽ ቆይቷል።

ይፋዊ ያልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እቀባ ተደርጓል የሚሉት የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ፤ ወደ ትግራይ መድረስ ከሚገባው እርዳታ 10 በመቶ ብቻ ለተረጂዎች መቅረቡን በመግለጽ በክልሉ ረሃብ ጉዳት እያስከተለ ነው ብለው እንደሚያስቡ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በሠሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነትና የተከተለውን ሰብአዊ ቀውስ ተከትሎ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባለፉት አስር ወራት ለስምንት ጊዜ ተሰብስቦ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል።