"ዓሳ ለማጥመድ ሄጄ አስከሬን አገኘሁ"

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ ካለው ከተከዜ ወንዝ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ቢያንስ 50 አስከሬኖች መውጣታቸው ተነግሯል።
በዚህም ሳቢያ ሱዳን በካርቱም የሚገኙትን የኢትዮጵያን አምባሳደር ጠርታ አስከሬኖቹ በተከዜ ወንዝ ዳርቻ መገኘታቸውንና ሟቾቹም ክትግራይ ክልል የሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች መሆናቸው እንደተገለጸላቸው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።
ጦርነቱን ሸሽቶ ወደ ሱዳን የተሰደደውን የህክምና ዶክተሩን ቴዎድሮስ ተፈራን ጨምሮ በርካታ ምስክሮች እንደሚያምኑት አስከሬኖቹ አማጺያኑ ከመንግሥት ሠራዊት ጋር እየተዋጉ ከነበረበት ከትግራይ ክልል የመጡ እንደሆነ ያምናሉ።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከወንዙ ውስጥ የተገኙት አብዛኞቹ አስከሬኖች ላይ የጥይት ቁስለትና እጆቻቸው ወደ ኋላ ታስሮ ነበር።
በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት ሐምዳይት የስደተኞች ካምፕ ውስጥ እየሰራ የሚገኘው ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደሚለው የተገኙት አስከሬኖች የወንዶችና የሴቶች ሲሆኑ አስከሬኖቹ ውሃ ውስጥ ቢያንስ ሰባት ቀናት ቆይተዋል።
አስከሬኖቹን ከወንዙ ውስጥ ያወጡ ሰዎችም ምስክርነታቸውን ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
"ዓሳ ላጠምድ ሄጄ አስከሬን አገኘሁ"
አቶ ዳዊት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ትግራይ ውስጥ ግጭቱ ሲቀሰቀስ የተከዜን ወንዝ ተሻሮ ነበር የተሰደደው። ኑሮን በስደተኝነት ሱዳን ውስጥ መምራት ከጀመረ አሁን አስር ወራት ተቆጥሯል።
አቶ ዳዊት ህይወት በስደት ላይ አስቸጋሪ ሲሆን ህይወቱን ከግጭቱ ለማትረፍ ተሻግሮት ከሄደው የተከዜ ወንዝ "ዓሳ ማጥመድ ጀመርኩ" ይላል። ኑሮውን ለመደገፍ ዓሳዎቹን በስደተኛ ካምፑ አካባቢና በሌሎች ስፍራዎች ለሚኖሩ ሰዎች ይሸጣል።
ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ እንደለመደው ዓሳ ለማስገር ወደ ወንዙ በሄደበት ጊዜ ግን "አስደንጋጭ ሁኔታ" ገጠመው። ዕለቱ በህይወቱ በእጅጉ ከደነገጠበት ቀኖች ሁሉ የበለጠው ነበር።
"ከጓደኛዬ ጋር ዓሳ እያጠመድን ሳለ አንድ ነገር ወደ ጀልባችን ሲቀርብ አየሁኝ። ወዲያውም በፊቱ ተደፍቶ የሚንሳፈፍ አስከሬን እንደሆነ አወቅን። በጣም ደነገጥን፣ ከዚያም አስከሬኑን አውጥተን ከወንዙ ዳር ቀበርነው። ያን ቀንም ዓሳ ላለማጥመድ ወሰንን። ነገር ግን ከ40 ደቂቃ በኋላ ሌላ አስከሬን ሲንሳፈፍ ተመለከትን። በጣም ተረበሽን፤ ያን ቀን ምግብ መመገብ አልቻልንም" ብሏል።
ሐምሌ 11 አንድ አስከሬን ሲያገኙ ሌሎች ሦስት ደግሞ በውሃው ሲወሰዱ ማየታቸውንና ሐምሌ 19 ደግሞ ሦስት አስከሬኖችን ከወንዙ ለማውጣት መቻላቸውንና አንድ ሌላ ደግሞ በውሃው መወሰዱን ዳዊት ለቢቢሲ ተናግሯል። ጨምሮም በውሃው የተወሰዱት አስከሬኖች ካወጧቸው ይበልጣሉ ይላል።
ከወንዙ ውስጥ ካገኟቸው አስከሬኖች መካከል አንደኛው አንገት ላይ የትግርኛ ጽሁፍ መነቀሱን የሚናገረው ዳዊት አስከሬኖቹ ጭንቅላታቸውና አንገታቸው ላይ በጥይት መመታታቸውን መመልከቱን ይናገራል።
"በአንድ ላይ የታሰሩ ሦስት አስከሬኖች"
በአንድ ቀን ውስጥ 25 አስከሬኖች ከተከዜ ወንዝ ሲወጡ እንደተመለከቱ የሚናገሩት አቶ ካህሳይ ከሟቾቹ መካከል ሴቶችና ህጻናት ይገኙበታል ብለዋል።
"እኔ እራሴ አንድ አስከሬን አውጥቻለሁ" ያሉት አቶ ካህሳይ የተመለከቷቸው 25 አስከሬኖች በሙሉ እርቃናቸውን ነበሩ። "ሦስት አስከሬኖችን ያገኘናቸው አንድ ላይ ታስረው ነበር" በማለት አንዳንዶቹ ጭንቅላታቸው ላይ ሌሎቹ ደግሞ ደረታቸው ላይ በጥይት መመታታቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
"አንዲት ሴት ከሁለት ህጻንት ልጆች ጋር በብርድ ልብስ ተሸፍና ያገኘን ሲሆን እጆቿም በገመድ ታስሮ ነበር. . . እጅግ አሰቃቂ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ እስከ ስድስት የሚደርሱ አስከሬኖች ከወንዙ ተገፍተው ወጥተው መገኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ካህሳይ፤ ከሁመራ፣ ከአደባይ፣ ከራውያ የመጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስባሉ።
የቢቢሲ ምንጮች የአስከሬኖቹ ሁኔታ ሟቾቹ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተገደሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለክታሉ። በተጨማሪም የተገኙት አስከሬኖች በምዕራብ ትግራይ በትግራይ ተወላጆች ላይ በተፈጸመ ግድያ ምክንያት የተገኙ እንደሚሆኑ ያምናሉ።
ይህንን በተመለከተ ባለፈው ነሐሴ ወር የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንደተናገሩት "እንዲህ አይነቱ ዜና ሆን ተብሎ የዓለም ተቋማትንና የዓለም ማኅበረሰብን ለማሳሳት የተቀናበሩ ናቸው። ነጭ ውሸት ነው። የአማራ ልዩ ኃይልም ሆነ ፋኖ እንዲህ አይነቱን ድርጊት አይፈጽሙም" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ሲኤንኤን ሱዳን ውስጥ ዋድ-ኤል-ሃይሎ ወደ ተባለው ስፍራ በመሄድ ጉዳዩን በተመለከተ ሰፊ ዘገባ ሰርቶ ነበር። ቡድኑም በአንድ ቀን በወንዙ ላይ ሦስት አስከሬኖች ሲንሳፈፉ መመልከቱን ዘግቧል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት ባለሙያዎች እየተንሳፈፉ የተገኙት አስከሬኖች ተገድለው ወደ ወንዙ የተጣሉ እንደሆነ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
"እጄን በጥይት ተመትቼ ቆስያለሁ"
ሱዳን ውስጥ ህክምና እየተሰጠው ያለው ተወልደ እሱና ሁለት ሰዎች ሁመራ ውስጥ ባለፈው ሐምሌ ወር 'ያለምክንያት ታስረንበት' ነበር ካለው እስር ቤት አምልጦ የተከዜን ወንዝ ሲሻገር በጥይት ተመቶ መቁሰሉን ለቢቢሲ ገልጿል።
"ጠዋት 12 ሰዓት አካባቢ ነበር። እንዳንንቀሳቀስ ሲነግሩን ባለንበት ተቀመጥን። ተነሱ ሲሉን ወደ ቁጥቋጦ ውስጥ ሮጥን። ሲተኩሱብን ግራ እጄን ተመትቼ ብዙ ደም ስለፈሰሰኝ ወደቅኩኝ። ጠዋት ባቅራቢያው ወዳለ ገዳም ሄጄ መነኮሳት ድንበር ተሻግሬ እንድሄድ ረዱኝ" ብለዋል።
ተወልደ ሁመራ ውስጥ ያለው ሁኔታ አደገኛ እንደሆነና ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ባለው "ቀበሌ 03 ውስጥ አምስት ሺህ ያህል የትግራይ ተወላጆች ታስረዋል" ይላል።
"የልዩ ኃይል አባላትና ፋኖዎች ከቤት ቤት በመሄድ የትግራይ ተወላጆችን ሲፈልጉ ሳይ ጥዬ ወጣሁ" ብሏል።
በሐምሌ ወር ቢቢሲ በሁመራ፣ በአደባይ፣ ኢድሪስ፣ እና ደግዋጉም ውስጥ ኢላማ ተደርገናል የሚሉ ሰዎችን አነጋግሮ ነበር። እነሱም አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ፣ ሕገ ወጥ እስርና ግድያ እንደሚፈጸም ገልጸው ነበር።
ይህንን በተመለከተ የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ በሰጡት ምላሽ ምዕራብ ትግራይ የሚባል ቦታ እንደማያውቁ ገልጸው፤ የቀረበውን ውንጀላ አጣጥለውታል።
"አንድም ትግርኛ ተናጋሪ መጥቶ ተፈጸመ ስለሚባለው ወንጀል ሪፖርት ያደረገ የለም" ብለዋል።
ጦርነቱ በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ሲጀመር በርካታ የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች በአማራ ክልል ቁጥጥር ስር ገብተዋል። ቦታዎቹ ከ30 ዓመት በፊት በሕገ ወጥ መንገድ በትግራይ ክልል ውስጥ ተካተው ቆይተው አሁን መልሰው መያዛቸውን ይናገራሉ።
ይህ ቦታ በአሁኑ ጊዜ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ቁጥጥር ስር ሲሆኑ የተወሰኑ የኤርትራ ኃይሎችም እንደሚገኙ ይነገራል።
ባለፈው ወር በአሜሪካ መንግሥት የወጣ አንድ ሪፖርት "በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳት እየተካሄደ ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ክሱን "ነጭ ውሸት" በማለት ውድቅ አድርጎታል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአማራ ክልል መስተዳደር ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ይፈጸማልና የዘር ማጽዳት እየተካሄደ ነው መባሉን አይቀበሉትም።












