ተከዜ ወንዝ ውስጥ የተገኘውን አስክሬን በማስመልከት ሱዳን የኢትዮጵያን አምባሳደር ጠርታ አነጋገረች

ተከዜ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ተከዜ ወንዝ ውስጥ የበርካታ ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ተከትሎ ሱዳን በካርቱም የሚገኙትን የኢትዮጵያን አምባሳደርን ጠርታ ማናገሯ ተነገረ።

ሱዳን የኢትዮጵያን አምባሳደር ጠርታ ባነጋገረችበት ወቅት ለአምባሳደሩ በወንዝ ውስጥ የተገኙት 29 አስከሬኖች የትግራይ ተወላጆች ስለመሆናቸው አስረድታለች ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።

ከሳምንታት በፊት በጥይት የተመቱ እና እጃቸው ወደኋላ የታሰሩ አስከሬኖች ወደ ሱዳን በሚፈሰው የተከዜ ወንዝ ውስጥ መገኘታቸው መዘገቡ ይታወሳል።

በወቅቱ የአገሪቱ ፖሊስ በሱዳን ሰቲት በኢትዮጵያ ደግሞ ተከዜ ተብሎ በሚጠራ ወንዝ ውስጥ የ28 ሰዎች አስከሬን መውጣቱን አስታውቆ ነበር።

ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የሰዎች አስክሬን በሱዳን በኩል ወንዝ ውስጥ የተገኘው ሐምሌ 26 እና ነሐሴ 27/2013 ዓ.ም. መካከል መሆኑን ለአምባሳደሩ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አስከሬናቸው የተገኙ ሰዎች ሕይወታቸው በምን ምክንያት እንዳለፈ ያለው ነገር የለም።

አምባሳደሩ ጥሪ ተደርጎላቸው ስለጉዳይ እንዲያውቁ የተገደረገው ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም. መሆኑ ተመልክቷል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ መግለጫ የሰዎች አስክሬን የተለየው ምሥራቅ ሱዳን ዋድ አል ሁላዋህ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ነው ይላል።

ተከዜ ወንዝ

የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፤ አስከሬኖቹ በተከዜ ወንዝ ውስጥ ከመታየታቸው በፊት የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ በትዊተር ገጹ ላይ "የህወሓት ፕሮፓጋንዳ አራጋቢዎች የሐሰት ምስሎችን እና ስዕላዊ ቅንብሮችን በመጠቀም ሐሰተኛ 'የሁመራ ጭፍጨፋ' ዘመቻ እንደገና በማነሳሳት ላይ ይገኛሉ" ሲል አስፍሮ ነበር።

ሁመራ የተከዜ ወንዝ የሚያልፍባት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኝ አካባቢ ናት።

በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ከአስር ወራት በፊት ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሱዳን መሸሻቸው ይታወሳል።

መንግሥት ወደ ሱዳን ደንበር የተሻገሩ ታጣቂዎች ከሱዳን ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሁም ወደ አማራ ክልል በመግባት ከህወሓት ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ሲል ሰኞ ዕለት መግለጫ አውጥቶ ነበር።

ይህን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) በሱዳን በሚገኙ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም እነዚህ ስደተኞች የት እንዳሉ ግን እንደማያውቅ ብሏል።

የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ይገባኛል በሚሉት የድንበር ቦታ እና በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት በመካከላቸው ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።

ኢትዮጵያ የትግራዩ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ በአልፈሽጋ የነበራትን ጦር ካንቀሳቀሰች በኋላ ሱዳን የድንበር ቦታውን ተቆጣጥራ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሱዳን የያዘችውን መሬት ለቅቃ እንድትወጣ ሲጠይቅ ቢቆይም የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን መሬቱ የሱዳን እንደሆነ በመግለጽ ለቀው እንደማይወጡ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊትም የሱዳን መሪዎች በአልፋሽጋ አካባቢ የገነቧቸውን መሠረተ ልማቶች አስመርቀው ነበር።

በሌላ በኩል ከሦስት ቀናት በፊት ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ከሱዳን ሰርጎ ለመግባት የሞከረ የህወሓት ቅጥረኛ ኃይልን ደመሰስኩ ማለቷ ይታወሳል።

የአገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ኮሎኔል ሰይፈ ኢንጊ፣ በሰዱን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገባ የተባለው ኃይል የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ጥቃት ለመሰንዘር እንደነበር አመልክተዋል።

ጨምረውም ቡድኑ የተለያዩ ፀረ ሰው እና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን ለማጥመድ ሞክሮ ነበር ስለማለታቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት አስታውቆ ነበር።