ጳጳሱ ከወሲብ ቀስቃሽ ፅሑፎች ደራሲዋ ጋር በፍቅር ወድቀው ሥራቸውን ለቀቁ

ስፔናዊው ጳጳስ

የፎቶው ባለመብት, Bishopric of Solsona

ባለፈው ወር ስፔናዊው ጳጳስ ዣቪዬር ኖቬል ሥራቸውን ሲለቁ የሮማን ካቶሊክ ቤተክርስትያን የሰጠችው ምክንያት ሌላ ነበር።

ቤተክርስትያኗ ጳጳሱ የለቀቁት በግላቸው ምክንያት ነው ካለች በኋላ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ታቅባለች።

ነገር ግን አሁን የስፔን መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩ ወዲህ ነው እያሉ ነው።

ጳጳሱ የለቀቁት ሰይጣናዊ ይዘት ያላቸው ወሲብ ቀስቃሽ ፅሑፎች ከምትፅፈው ተያቢ ጋር በፍቅር ወድቀው መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል።

ዣቪዬር ከ11 ዓመታት በፊት በ41 ዓመታቸው ካታሎኒያ ውስጥ ሲሾሙ በዕድሜ ትንሹ ጳጳስ ነበሩ።

ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ የሆኑ ሰዎች መቀየር ይችላሉ ብለው ከማመን አልፎ ሰይጣን የማስወጣት ተግባር ይፈፀሙ ነበር።

በስፔን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዘንድ እየተመነደገ እንዳለ የጌታ ሰው ነበር የሚቆጠሩት። ነገር ግን ሥራቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው ሲነሳም ብዙዎች ተገርመር ነበር።

ከቫቲካን ባለሥልጣናት እንዲሁም ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ብዙ ጊዜ ተገናኝተው ነበር ይባላል።

ፅንስ ማቋረጥን በተመለከተ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ይከተላሉ ተብለው ቢተቹም የካታሎኒያ ነፃነትን በተመለከተ ያላቸው አስተሳሰብ አነጋጋሪ ነበር።

ሪሊጂን ዲጂታል የተሰኘው ጋዜጣ ጳጳሱ የስነ-ልቡና ባለሙያና ወሲብ ቀስቃሽ መፅሐፎች ደራሲ ከሆነችው ሲልቪያ ካባዮል ጋር በፍቅር ወድቀዋል ብሎ ሲዘግብ ብዙዎች አጀብ ተሰኝተው ነበር።

ጋዜጣው አክሎ ጵጵስናቸውን ጥለው የኮበለሉት ግለሰብ ባርሴሎና አካባቢ የግብርና ባለሙያ ሆነው ለመቀጠር ሥራ እየፈለጉ ነው በሚል አስነብቧል።

ፀሐፊዋ የምትፅፋቸው ፅሑፎች በሰው ስቃይ መደሰት፣ የወሲብ ጥማትና ከጥሩና መጥፎ ጋር ትግልን የሚያስነብቡ ናቸው።

ፈጣሪና ሰይጣንን ገፀ ባሕርያዊ አድርጋ የምትተይበው የሥነ-ልቡና ባለሙያ የአንባቢዎቿን እምነትና አስተሳሰብ በመናጥ ትታወቃለች።

የ52 ዓመቱ የቀድሞው ጳጳስም ሆነ ደራሲዋ እስካሁን ድረስ ስለዘገባው ያሉት ነገር የለም።

ያገለግሉበት የነበረው ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪዎች 'ይህ የሳቸውና የሳቸው ብቻ ግላዊ ጉዳይ ነው' ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

የጳጳሱ መኮብለል የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ሕግጋት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል። ቤተ-ክርስትያኗ ለአገልጋዮች ፇታዊ ግንኙነት ማድረግን አትፈቅድም።

ጳጳስ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ወጣት ሳሉ ከአንዲት 18 ዓመት ታዳጊ ጋር በፍቅር ወድቀው ትዳር ሊይዙ አስበው ነገር ግን ሐሳባቸውን ቀይረው ቤተ-ክርስትያንን ወደ ማገልገል መሄዳቸውን ተናግረው ነበር።