በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ከ2800 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መሰንዘራቸው ተገለጸ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ

የፎቶው ባለመብት, Information Network Security facebook

በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር [የመረጃ መረብ] ጥቃት ሙከራዎች በእጥፍ መጨመራቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጄንሲ አስታወቀ።

በዚህም እየተጠናቀቀ ባለው በ2013 ዓ.ም ብቻ ከ2 ሺህ 800 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መሰንዘራቸውን ኤጀንሲው ገልጿል።

የሳይበር ጥቃቶቹ ኢላማ ያደረጉት የፋይናንስ፣ የህክምና፣ ሚዲያ እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች በአገሪቱ ያሉ ወሳኝ መሰረተ-ልማቶችን እንደነበረ ኤጀንሲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

የጥቃቶቹ ሙከራዎች መነሻቸው ከተለያዩ የዓለም አገራት በሚገኙ የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች የተሰነዘሩ እንደነበሩም ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት 1 ሺህ 80 አካባቢ የሳይበር ጥቃቶች የተሰነዘሩ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት በእጥፍ ለመጨመሩ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉም የኤጀንሲው ብሔራዊ የሳይበር ጥቃት የአደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ዲቪዢን ኃላፊ አቶ ሰብለወይን ጸጋዬ አመልክተዋል።

ኃላፊው ለጥቃቶቹ መጨመር እንደምክንያት የተለያዩ ተቋማት ከዚህ ቀደም ከነበረው የኢንተርኔት አጠቃቀማቸው መስፋቱ፣ ከሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ ጫናዎች መፈጠራቸው፣ አገሪቷ በተለያዩ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆንዋና ተቋማትም የሳይበር ደኅንነት ጋር በተያያዘ ያላቸው ክፍተት መሆኑን በዋናነት ጠቅሰዋል።

በዓመቱ ውስጥ ከተሰነዘሩት የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 75.2 በመቶ ምላሽ እንደተሰጠባቸና ቀሪዎቹ ደግሞ ምላሽ እየተሰጠባቸው እንደሆነ ተገልጿል።

የሳይበር ጥቃት ሙከራዎቹ በድረ-ገፅ ላይ 33.26 በመቶ፣ በአጥፊ ሶፍትዌሮች (ማልዌር) አማካኝነት 29.43 በመቶ፣ በመሠረተ ልማት ቅኝቶች 18.7 በመቶ እንዲሁም ወዳልተፈቀደ ሲስተም ሰርጎ መግባት 16.15 በመቶ እና የሳይበር መሠረተ-ልማቶችን ሥራ ማቋረጥ ደግሞ 1.8 በመቶ ጥቃቶች መከሰታቸውን ሃላፊው አስረድተዋል።

አስፈላጊው ቁጥጥርና እርምጃ ባይወሰድ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎቹ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳትም ሊያደርሱ ይችሉ ነበር ተብሏል።

"እነዚህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ቢደርሱ ኖሮ በተቋማት እና በአገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የሥነ ልቦና ጫና ከፍተኛ ነበር" ብለዋል ኃላፊው።

ኤጀንሲው ከወራት በፊት በኢትየጵያ 37 ሺህ በሚሆኑ ኮምፒውተሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈፀም ሙከራዎች እየተደረጉ ነው ሲል አስታውቆ ነበር።

በወቅቱም ይህንን ጥቃት ለመፈፀም እየሞከረ ያለው 'ሳይበር ሆረስ ግሩፕ' የተባለ የመረጃ ሰርሳሪ ቡድን ነው ብሏል።

ኤጀንሲው "ብላክ ፒራሚድ ዋር" የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲስ ቫይረስ 37 ሺህ በሚደርሱ የአገሪቱ ኮምፒውተሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ለማድረስ እየሞከረ መሆኑንም ገልፆ ነበር።

ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም መሰረታቸውን ከግብጽ ያደረጉ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ተቋማት የመረጃ መረብ መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረግ ሞክረው እንደነበር መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ በወቅቱ እንዳስታወቀው በሦስት የተለያዩ ቡድኖች አማካይነት የተሞከረው የመረጃ መረብ ጥቃት በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ አመልክቶ ነገር ግን በኤጀንሲው አማካይነት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጾ ነበር።

ኤጀንሲው አሁን ባወጣው መግለጫ ቁልፍ የሳይበር መሰረተ-ልማቶችን እና የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ የሚያጋጥማቸውን የሳይበር ጥቃቶች የመከታተል እና ለሚፈጠሩ ጥቃቶች ምላሽ የመስጠት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ አስታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተቋማቱ የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት፣ የሰው ኃይላቸውን በዘርፉ የሰለጠነ እና ብቁ ማድረግ እንዲሁም ተገቢ እና አስፈላጊ የሆነ የሳይበር ደኅንነት ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ እንደሚገባ ኃላፊው ጠቁመዋል።