በኢትዮጵያ 37 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈፀም ሙከራዎች አሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Information Network Security facebook
በኢትየጵያ 37 ሺህ በሚሆኑ ኮምፒውተሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈፀም ሙከራዎች እየተደረጉ ነው ሲል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታውቋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ በማኅበራዊ የትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ ይህንን ለመፈፀም እየሞከረ ያለው 'ሳይበር ሆረስ ግሩፕ' የተባለ የመረጃ ሰርሳሪ ቡድን ነው ብሏል።
ቡድኑ አዲስ የኮምፒውተር ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ኮምፒውተሮች ላይ ለመልቀቅ ዝግጅት እንዳደረገ እንደተደረሰበት መግለጫው አክሏል።
ኤጀንሲው እንደገለፀው ቫይረሱ "ብላክ ፒራሚድ ዋር" የሚል ስያሜ እንደተሰጠውና 37 ሺህ በሚደርሱ የአገሪቱ ኮምፒውተሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ለማድረስ እየሞከረ መሆኑን ገልጿል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ቡድኑ ያነጣጠረባቸው እነዚህ 37 ሺህ ኮምፒውተሮች የት እንደሚገኙ፣ የማን እንደሆኑ ወይም ዝርዝር ጉዳዮችነም አላስቀመጠም።
ቡድኑ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በአገሪቱ ላይ ያሉ ድረ-ገፆችን የመበርበር ሙከራ ሲያደርግም መቆየቱንም ቢቢሲ ከኤጀንሲው ካገኘው መረጃ መረዳት ተችሏል።
ተቋሙ ቡድኑ የትኞቹን ድረ-ገፆች ላይ የመበርበር መከራ እንዳከናወነ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ሆኖም "ሁሉም የሳይበር ምህዳር ተጠቃሚዎች ተገቢውን የሳይበር ደኅንነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ" በማሳሰብ ምክሩን አስተላልፏል።
ኤጀንሲው ከዚህ በፊት መሰረታቸውን ከግብጽ ያደረጉ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ተቋማት የመረጃ መረብ መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረግ ሞክረው እንደነበር መግለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በወቅቱ እንዳስታወቀው በሦስት የተለያዩ ቡድኖች አማካይነት የተሞከረው የመረጃ መረብ ጥቃት በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ አመልክቶ ነገር ግን በኤጀንሲው አማካይነት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጾ ነበር።












