የፀጥታው ምክር ቤት በግድቡ ጉዳይ የቱኒዚያን ሐሳብ እንዳይቀበል ኢትዮጵያ ጠየቀች

የመንግሥታቱ ድርጅት የሕዳሴ ግድቡን ጉዳይ በተመለከተ የቱኒዚያን ምክረ ሐሳብ እንዳይቀበል ኢትዮጵያ ጠየቀች።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ጋር ትላንት ነሐሴ 20/2013 ዓ.ም ባደረጉት ውይይት የቱኒዚያ ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት እንዳያገኝ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በማኅበራዊ ድረ ገጾቹ እንደገለጸው፤ በውይይቱ የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ፤ የግድቡ ጉዳይ ለፀጥታው ምክር ቤት መቅረብ የለበትም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ተወስዶ ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት ዋና አሸማጋይነት እንዲፈታ ውሳኔ መሰጠቱን አስታውሰው፤ የቱኒዚያ ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት እንዳያገኝ ጠይቀዋል።

የምክር ቤቱ አባል ሆነችው ቱኒዚያ በድጋሚ ልታስገባ ያሰበችው ውሳኔ ሐሳብ የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት የሚጋፋ እንደሆነ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ግብፅ እና ሱዳን ጉዳዩን ባላስፈላጊ ሁኔታ ወደ ፖለቲካዊ ጡዘት እየወሰዱት እንደሆነም አክለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የታችኛው ተፋሰስ አገራት በአፍሪካ ሕብረት የበላይነት እየተካሄደ ያለውን ድርድር እንዲደግፉ ጫና እንዲያሳድርም ጠይቀዋል።

ቱኒዚያ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስለ ገድቡ ጉዳይ ምክረ ሐሳብ ስታቀርብ ይህ ሁለተኛዋ ነው። ከዚህ ቀደም ያስገባችው ሐሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ቱኒዚያ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ በድጋሚ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ልታስገባ መሆኑን መንቀፋቸው አይዘነጋም።

የላይኛው ተፋሰስ አገራት አምባሳደሮች ከኢትዮጵያው ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ጋር ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም. ውይይት አድርገው ነበር።

አምባሳደር ሬድዋን "አንዲት የአፍሪካ አገር ይህን የማይጠቅም እርምጃ መውሰዷ የግድቡን ግንባታ በተመለከተ ሦስቱ አገራት እያደረጉ ያሉትን ድርድር ከግምት ያላስገባ ነው። የላይኛው ተፋሰስ አገራት በፍጹም ሊቀበሉት አይገባም" ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መግለጫ ጠቁሟል።

ከወራት በፊት በግብፅ እና በሱዳን ጥሪ የግድቡን ግንባታ በተመለከተ የተሰበሰበው የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፤ በዋናነት የአፍሪካ ሕብረት እንዲያሸማግል ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል።

ቱኒያ እና የሕዳሴ ግድቡ

ቱኒዚያ ከዚህ ቀደም ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የጻፈችው ደብዳቤ "ለግብፅ ያደላ" እንደሆነ በኢትዮጵያ በኩል ሲተች ነበር።

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ባካሄደች ሰሞን ምክር ቤቱ ስብሰባ ከማድረጉ በፊት ቱኒዝያ ለፀጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት እንድታቆም ጠይቃለች።

ቱኒዚያ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ቡድን የወቅቱ አባል ናት።

የቱኒዚያ ምክረ ሐሳብ ሦስቱ አገራት በአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አማካይነት በስድስት ወራት ውስጥ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ይላል።

ስምምነቱ "ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ችግር ውስጥ በማይከት መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጯ የሚሆነውን ሕዳሴ ግድቡን መገንባት የምትቀጥልበት መንገድን" የተመለከተ ነው።

ኢትዮጵያ ግን የሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መወሰዱን እንዲሁም ቱኒዚያ አባል የሆነችበት የአረብ ሊግ አገራትን ጣልቃ ገብነት በተደጋጋሚ ኮንናለች።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ 'ኢጂፕት ቱደይ' የተሰኘው ድረ ገጽ ባወጣው ዘገባ "ቱኒዚያ የምትፈልገው የሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ሄዶ እንዲጋጋል ሳይሆን ሦስቱ አገራት ሕጋዊ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ነው" ብሏል።

በግብፅ የቱኒዚያ አምባሳደር የሆኑትን መሐመድ ቢል የሱፍ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ቱኒዚያ በሕዳሴ ግድቡ ላይ ያላት አቋም ግብፅን "የሚደግፍ" ሳይሆን "ለእህት አገር" ያላትን ኃላፊነት ለመወጣት ያለመ ነው።

ግድቡና የተፋሰሱ አገራት

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው እንዲሁም ስለ ግንባታው ለዓመታት የተወዛገቡትም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ናቸው። ሆኖም ግን ሌሎችም የተፋሰሱ አገራት በጉዳዩ ላይ ተሰሚነት አላቸው።

የዓባይ ተፋሰስ አገራት ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናቸው።

በዋነኛነት ግብፅ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ባላማከለ መልኩ የዓባይ ወንዝን ለመጠቀም ፍላጎት አላት በሚል በተደጋጋሚ ተወቅሳለች። የአረብ ሊግ አገራት በሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ጣልቃ እንዲገቡ ማድረጓንም ኢትዮጵያ በበጎ አታየውም።

ዓባይን በዋነኛነት ተከፋፍለው የያዙት ግብፅ እና ሱዳን ሲሆኑ ግብፅ 66 በመቶ ሱዳን ደግሞ 22 በመቶ ድርሻ ወስደዋል። ኢትዮጵያ ግን ምንም ድርሻ የላትም።

ይህ ስምምነት በቅኝ ግዛት ወቅት በእንግሊዝ አደራዳሪነት የተደረገ በመሆኑ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ብትነቅፈውም ግብፅ እና ሱዳን የኢትዮጵያን ተቃውሞ ችላ ሲሉት ቆይተዋል።

ግብፅ በላይኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላት ሲሆን፤ በዚህ ስምምነት ላይ ኢትየጵያ ምንም ተሳተፎ አልነበራትም።

በነጭ ዓባይ የሚባለው ከማዕከላዊ አፍሪካዋ ግሬት ሌክስ ተነስቶ በታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ይፈሳል። ጥቁር ዓባይ ከኢትዮጵያ አንስቶ በሱዳን በኩል ወደ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ይፈሳል።

ሁለቱ ወንዞች በሱዳን መዲና ካርቱም አካባቢ ተገናኝተው አንድ ላይ ወደ ግብፅ ይፈሳሉ።

ግብፅ የዓባይ ወንዝ የሕይወት መሠረቷ ነው። ለኢትዮጵያም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ 6450 ሜጋ ዋት ኃይል ማምረት ትችላለች።

ከአገር ውስጥ ፍጆታ የሚተርፈውን (2000 ሜጋዋት ገደማ) ለጎረቤት አገራት በመሸጥ በዓመት እስከ 580 ሚሊዮን ዶላር እንደምታተርፍም ይገመታል።

ግብፅ የግድቡ የውሃ ሙሌት ወደ አገሪቷ የሚፈሰውን የውሃ መጠን እንደሚቀንሰው እና ሕዝቧን ለረሃብ እንደሚያጋልጠው ትከራከራለች።

ሱዳን ከግድቡ ግንባታ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማግኘቷ ባሻገር በካርቱም የሚከሰተውን ጎርፍ ከመከላከል አንጻርም ከግድቡ ተጠቃሚ ብትሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ ይልቅ ወደ ግብፅ የሚያደላ አቋም ስታንጸባርቅ ተስተውሏል።

ግብፅ የዓባይ ተፋሰስ አገራትን ከጎኗ ለማሰለፍ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች።

ከወራት በፊት ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከጂቡቲ፣ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ከሩዋንዳ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከብሩንዲ፣ ከታንዛንያ እና ከኡጋንዳ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ማድረጓም ከግድቡ ግንባታ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንሚችል ተንታኞች ጠቁመዋል።