በምሥራቅ ወለጋ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

ኪራሙ ካርታ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም ጀምሮ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት እና ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች እና የዞኑ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት በአካባቢው መንግሥት ኦነግ ሸኔ እያለ የሚጠራቸው ታጣቂዎች ቀደም ብሎም እንደሚንቀሳቀሱ አስታውሰው፤ በነዋሪዎች ላይ ግድያውን የፈጸመው ይህ ታጣቂ ቡድን መሆኑን ይናገራሉ።

ተወልደው ያደጉት እዚያው ምስራቅ ወለጋ ኪራሙ እንደሆነና የአማራ ብሔር ተወላጅ እንደሆኑ የሚናገሩት ነዋሪው፤ በስፍራው የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከስፍራው መውጣቱን ተከትሎ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

"በእርግጥ ልዩ ኃይሉ መስዋዕትነት አልከፈልም አንልም፤ ግን ኃይላቸውና ትጥቃቸው ተመጣጣኝ አልነበረም። በነሐሴ 11 ልዩ ኃይሎቹ አካባቢውን ለቀው ሲወጡ ኦነግ ሸኔ በ12 ወረራ ጀመረ። ከስፍራው የነበሩ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ ማንም የተረፈ የለም። ንጹሀን ተጨፍጭፈው ቀሩ። ንብረት ሁሉ ተቃጥሎ ወደመ" ይላሉ።

ነዋሪው በጥቃቱ የሞቱ ሰዎች በመቶዎች እንደሚቆጠሩ የተናገሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ8 ሺህ በላይ ሰው ተፈናቅሎ በወረዳው አጎራባች ቀበሌ ላይ እንደሚገኝ አመልክተው "ለተፈናቃዩ ሕዝብ የደረሰ እርዳታ የለም" የለም በማለት በችግር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ወቅቱ ክረምት በመሆኑ በየወንዙ የወዳደቀ አስክሬን ተፈልጎ በሦስተኛው ቀን 150 አስክሬን ተቀብሯል። አስክሬኑ ያልተገኘና ማሕበረሰቡ የጠፋ ቤተሰብ እንዳለው ሲጠየቅ ግን አጠቃላይ ወደ 300 የሚሆን ሰው እንደተጨፈጨፈ ነው የተረዳነው" ይላሉ ነዋሪው።

አካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈፀምበት በመሆኑ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ 'መታጠቅ የሚችል ነዋሪ ታጥቆ ራሱን እንዲከላከል ተፈቅዶ ነበር' የሚሉት እኝህ ነዋሪ፤ "ጥቃቱ የተጀመረው አብዛኛው የአማራ ተወላጅ የሚኖርበት ቦታ ላይ ነው። ሰው ሕይወቱን ያተረፈው የታጠቁ አርሶ አደሮች ባሉበት አካባቢ ነው። እኛም የወጣነው እነርሱ ሲታኮሱ ነው። የታጠቁ አርሶ አደሮች ቁጥር ትንሽ በሆነበት ግን ከበባ ተደርጎ ንጹኃን ሰዎች ተገድለዋል።" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የአባቴ ወንድምና የእናቴ እህት ከእነቤተሰቦቻቸው ሞተዋል። የእኔ ቤተሰቦች ግን ፈጣሪ ፈቅዶ ወጥተውልኛል" ብለዋል ነዋሪው።

10 የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እንዲሁም ሦስት ሚሊሻዎች መገደላቸውንም ነዋሪው አክለዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ተስፋ ለቢቢሲ እንደገለጹት ከአምስት ቀናት በፊት በአካባቢው ግጭት እንደነበረ አረጋግጠው፤ ጉዳት የደረሰው "የጁንታው ተላላኪ በሆነው ሽፍታው ሸኔ እና መሣሪያ በታጠቁ የአማራ ብሔር ጽንፈኞች" ምክንያት ነው።

ጨምረውም "ጥቃቱን በዋናነት የሸኔ ሽፍታዎችና የጁንታው ተላላኪዎች ናቸው በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ ላይ ተኩስ በመክፈት የፈጸሙት። የታጠቁ የአማራ ብሔር ጽንፈኞችም አሉ። አሁን ግን ግጭቱ ቆሟል" ብለዋል።

"በዋናነት በኦሮሞ እና አማራ ሕዝብ ላይ ተኩስ የከፈተው ሽፍታው ሸኔ ነው። የታጠቁ የአማራ ብሔር ጽንፈኞችም አሉ። ሁለቱ ቡድኖች ናቸው በሁለቱ ብሔር ላይ ጉዳት ያደረሱት" ብለዋል የዞኑ አስተዳዳሪ።

አስተዳዳሪው አቶ አለማሁ እንዳሉት "በአሁኑ ወቅት የፀጥታ አካላት ገብተው እርምጃ እየወሰዱና ሕዝቡን እያረጋጉ ነው። እስካሁን ድረስ በግጭቱ የሞተውና የተጎዳው ሰው ቁጥር እየተጣራ ነው። ውጤቱ ሲደርስ እናሳውቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።

በስፍራው ይንቀሳቀሳሉ ያሏቸው "ሽፍታው ሸኔ እና የታጠቁ የአማራ ብሔር ጽንፈኞች " የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ተናግረው፤ "እነዚህ ሁለት ቡድኖች እርስ በእርሳቸው ተታኩሰዋል። ሕዝብም ላይ ተኩሰዋል" ብለዋል አስተዳዳሪው።

የሁለቱ ቡድን ዓላማ "ለብዙ ዓመታት አብሮ በሰላም የኖረን ብሔር ማጋጨት ነው" ያሉት አቶ አለማየሁ፤ በግጭቱ የሰዎች ሕይወት ማለፉን እና በርካታ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው መረጋጋት መኖሩን እና ከቀያቸው የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ አክለዋል።

ሌላኛው ያነጋገርናቸው ነዋሪ ደግሞ በአካባቢው በኦሮሞና በአማራ ተወላጆች መካከል ግጭት እንደነበር ተናግረው ጉዳት የደረሰውም በዚሁ ምክንያት ነው ብለዋል።

"በአማራ እና በኦሮሞ ማኅበረሰብ መካከል ግጭት ነበር። ከድሮ ጀምሮ የሚኖሩ የአማራ ማኅበረሰቦች ነበሩ። ከዚህ ቀደም በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ወደ ክልላቸው ከሄዱ በኋላ ሴቶች እና ሕጻናትን ትተው ወደ አካባቢው ተመልሰው በመምጣት እዚያ ከሚኖር የኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋር ተጋጭተዋል" ይላሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጁ።

ነዋሪው ይህን ይበሉ እንጂ የዞኑ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከአማራ ክልል ወደ አካባቢው የገባ ታጣቂ የለም።

"በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ብዙ ነገር ይወራል። በተለያየ መንገድ ብሔሮች እንዲጣሉ ይደረጋል። ነገር ግን ከሌላ አካባቢ ገቡ ስለተባሉት ታጣቂዎች ምንም ማስረጃ የለም። ካለም ወደፊት እንናጣራለን" ብለዋል የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ተስፋ።

ቢቢሲ በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ባደረገው ሙከራ ከተለያዩ ወገኖች መጠኑ የተለያየ አሃዝ ያገኘ ሲሆን፤ ነገር ግን በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

በንብረትም በኩል ቤቶች መቃጠላቸው የተነገረ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከጥቃቱ ሽሽት ቤት ንብረታቸውን ትተው ወደ አቅራቢያ አካባቢዎች መሄዳቸው ተነግሯል።

መንግሥት ሸኔ የሚለውና በሽብርተኛነት የተፈረጀው እንዲሁም በቅርቡ ከህወሓት ጋር ጥምረት መፍጠሩን ያሳወቀው የኦሮሞ ነጻነት ጦር አሁን ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊት ጥቃት መፈጸማቸው አይዘነጋም።