ሊዮኔል ሜሲ ለፓሪስ ሴንት ዠርሜን ለመጫወት ተስማማ

ሊዮኔል ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና በድንገት መውጣቱን ተከትሎ የፈረንሳዩ ክለብ ለመቀላቀል በሁለት ዓመት ኮንትራት መስማማቱን የቢቢሲ ስፖርት አምድ ጸሐፊው ጊለም ባላግ ተናገረ።

ስምምነቱን ለማጠናቀቅ ሕክምና ማጠናቀቅ ብቻ ይቀረዋል።

የ34 ዓመቱ የአርጀንቲና አምበል በላሊጋ የፋይናንስ ፍትሃዊ ጨዋታ ህግ መሰረት አዲስ ውል ለመፈረም ባለመቻሉ በብቸኝነት የተጫወተብትን ባርሳን ለመልቀቅ ተገዷል።

የማውሪሲዮ ፖቸቲኖው ፒኤስጂ ባለፈው የውድድር ዘመን በሊግ 1 ከሊል በመቀጠል ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።

ባላግ በቢቢሲ ሬዲዮ 5 ቀጥታ ስርጭት ላይ "ሁሉም ነገር ተረጋግጧል። ሊዮኔል ሜሲ የፒኤስጂ ተጫዋች ይሆናል። ይህ ነው። ባለፉት ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የተከሰተ ነው" ብሏል።

"ሃሳቡ የእግር ኳስ ህይወቱን በባርሴሎና ማድረግ ነበር። . . . ከዚያ በኳታር የዓለም ዋንጫ ጥሩ ነገር ማድረግ ነው።"

ከዘመኑ ታላላቅ ተጫዋቾች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ሜሲ በ 13 ዓመቱ ለተቀላቀለበት ባርሳ 778 ጨዋታዎችን አከናውኖ 672 ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል።

የባላንዶርን ሽልማት ስድስት ጊዜ በማሸነፍ ባለክብረወሰን ሲሆን ከካታላኑ ክለብ ጋር 35 ዋንጫዎችን አንስቷል።

ሜሲ በፒኤስጂ ከቀድሞው የክለቡ አጋሩ ኔይማር ጋር ይገናኛል።

ሜሲ፤ ጆርጂንዮ ዋይናልደም፣ ሰርጂዮ ራሞስ እና ግብ ጠባቂው ጂያንሉጂ ዶናሩማ ተከትሎ የፒኤስጂ አራተኛው የነፃ ዝውውር ፈራሚ ይሆናል።

ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አክራክ ሃኪሚም ከኢንተር ሚላን የፓሪሱን ክለብ ተቀላቅሏል።

ስምምነቱ በፍጥነት ከተጠናቀቀ ቅዳሜ የመጀመሪያውን የፒኤስጂ ጨዋታውን ከስትራስቡርግ ጋር ማድረግ ይችላል።