ለትግራይ በቀን 100 የእርዳታ መኪኖች ያስፈልጋሉ- ተመድ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በረሃብ አፋፍ ያሉ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ በቀን ምግብና መድኃኒት የጫኑ አንድ መቶ የእርዳታ መኪኖች እንደሚያስፈልጉ የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ ተናግረዋል።
አስተባባሪው ትግራይን በቅርቡ የጎበኙ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በጄኔቫ በሰጡት መግለጫ በክልሉ ዕርዳታ ለማድረስም ሰብዓዊ የተኩስ አቁም አስፈላጊ ነው ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት 5.2 ሚሊዮን ህዝብ ወይም 90 በመቶ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ አስቸኳይ ህይወት አድን ዕርዳታ ያስፈልገዋል ብሏል።
የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ኃላፊ ሰማንታ ፓወር በሰሞኑ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የእርዳታ ተደራሽነቱ ጉዳይ የበለጠ የሚያሳስብ ሆኗል ብለዋል።
በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስም ለመፍታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ500-600 እርዳታ የጫኑ መኪኖች በየሳምንቱ ትግራይ መግባት አለባቸው ቢልም ከሁለት ቀናት በፊት በነበረው መረጃ መሰረት 153 የጭነት መኪኖች ወደ ትግራይ ገብተዋል።
በተመድ መሰረት በባለፉት ሳምንታት 1500 የጭነት መኪኖች መግባት ቢያስፈልግም እስካሁን የገባው 153 ነው ይህም ማለት ከሚያስፈልገው 10 በመቶ ነው ተብሏል።
በተወሰነ መልኩ ስርዓቱና ፈቃዶች ላይ መሻሻል ቢታይም የእርዳታ መዘግየትና ህይወት አድን እርዳታዎችን ለማድረስ ማየት የሚፈለገውን ለውጥ ማየት አልተቻለም ብለዋል።
አስተባባሪው በትግራይ አስከፊ የሰብዓዊ ሁኔታ መመልከታቸውንም እንዲም በጦርነቱ ህይወታቸው የተመሰቃቀለ ዜጎችም ጋር ተወያይተዋል ብሏል።
"በጦርነቱ ምክንያት የነበራቸውን ሁሉ ያጡ ሰዎች አግኝቻለሁ። መኖሪያቸውንና የእርሻ መሬታቸውን እንዲሁም መንደሮቻቸውንና ከተማቸውን ጥለው የተሰደዱ። በሃውዜን ቤታቸው ተቃጥሎ ሰብላቸው የተዘረፈ ቤተሰብ ጎብኝቻለሁ። እስካሁን ድረስ መጠለያም ሆነ ምግብ የሌላቸውም ቤተሰቦችን ማየትም ሆነ የጥፋቱን መጠን መመልከት ልብ ይሰብራል" ብለዋል።
የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ በትግራይ ጉብኝታቸው ወቅት አሰቃቂ ጥቃት የደረሰባቸውን ግለሰቦችንም ማናገራቸው ተጠቅሷል።
ከዚህም በተጨማሪ የዜጎች መሰረታዊ ልማት የሆኑ እንደ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታልና ውሃ አገልግሎቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዴት እንደወደሙም በአይናቸው ታዝበዋል ተብሏል።
በክልሉ አስከፊ የምግብ እጥረት እንዳለ ገልፀው ረሃብም እውነተኛ ስጋት እንደሆነም ተነግሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታትን ዕቅድ ዕደግፋለሁ ማለቱም ተገልጿል።
የህወሃት ኃይሎች ወደ አጎራባቹ ክልል አማራ ጦርነቱን እያሰፉ ሲሆን በትናንትናውም ዕለት በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቅርስ ሆና የተመዘገበችውን የላሊበላን ቅርስ መገኛ ከተማ ተቆጣጥረዋል።
የሰብዓዊ ዕርዳታ ኃላፊው የተባበሩት መንግሥታት በሰብዓዊ ቀውሱ ድርጅታቸው ገለልተኛ መሆኑን አስምረው የአሜሪካ ጥሪን በመድገም የህወሃት ኃይሎች ከአማራ ክልል እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የትግራይን ህዝብ ህልውና ለማረጋገጥ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ግጭቱን ማስቆም ነው ብለዋል።
የህወሃት ኃይሎች በበኩላቸው ከአጎራባች ክልሎች እንዲወጡ የቀረበውን ጥሪ ውድቅ ማድረጋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
የህወሃት ቃለ አቀባይ ጌታቸው ረዳን በሰብዓዊ ተደራሽነት ላይ ያሉ ገደቦችን በመጥቀስ "በትግራይ ያለው መዘጋት (ብሎኬድ) እስካልተከፈተ ድረስ ምንም ነገር አይከሰትም" ማለታቸን ዘገባው አስነብቧል።
በተያያዘ ዜና የምግብ እርዳታ የጫኑ 220 መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል መቀለ በባለፉት ሶስት ቀናት መድረሳቸውን የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል።
በሐምሌ 28 ቀን ከተገለፀው በተጨማሪ የምግብ ዕርዳታን የጫኑ 63 መኪኖች በዛሬው ዕለት ወደ መቀለ ደርሰዋል ተብሏል።












