መንግሥት ሙሉ ኃይሉን በማሰማራት እርምጃ ለመውሰድ እየተገደደ መሆኑን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የህወሓት አማጺያን እየፈጸሙት ያለው ጥቃት መንግሥት ሙሉውን የመከላከያ ኃይሉን በማሰማራት እርምጃ ለመውሰድ እያስገደደው መሆኑን አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አርብ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ የህወሓት ቡድን በአጎራባች ክልሎች ውስጥ በሚሰነዝራቸው ጥቃቶች ሳቢያ የፌደራሉን መንግሥት ትዕግስት እየተፈታተነው መሆኑን አመልክቷል።
በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ መንግሥት በተናጠል የወሰደው የተኩስ አቁም እርምጃ አወንታዊ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ የአገሪቱን አንድንትና ሉአላዊነትን ለመከላከል መላውን ሠራዊቱን በማንቀሳቀስ እርምጃ ይወስዳል ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለስምንት ወራት በትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ላወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም ታማኝ ሆኖ ቢቆይም በህወሓት በኩል ግን ተቀባይነት አለማግኘቱን መግለጫው አመልክቷል።
ከዚህ ባሻገርም አማጺው ቡድን በአጎራባች የአፋርና የአማራ ክልሎች ላይ ጥቃት በመክፈት "በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ ከ300 ሺህ በላይ የሚሁኑት ደግሞ ተፈናቅለዋል" ሲል ከሷል።
ይህ የህወሓት ጦረኝነት መንግሥት ሰላም ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት እንዳይሳካ እንዳደረገውና አገርን የመከላከል የሞራል፣ የሕግና ፖለቲካዊ ግዴታ ስላለበት እርምጃ ለመውሰድ እየተገደደ ነው ብሏል።
መግለጫው ኃላፊነት የጎደለው ያለው የህወሓት ቡድን በሚወስዳቸው እርምጃዎች ለሰብአዊነት ሲባል በወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ላይ የሚገኘውን የፌደራሉን መንግሥት ትዕግስት እየተፈታተነ በመከላከል ላይ ያተኮረውን አቋሙን እንዲቀይር እየገፋው መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ዛዲግ አብረሃ ከቀናት በፊት ለቢቢሲ እንደተረናገሩት፤ መንግሥት ትዕግስት ላይ መሆኑንና ጊዜው ሲደርስ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ "ትዕግስታችን ሲሟጠጥ ከእያንዳንዱ አካባቢ ጠራርገን እናስወጣቸዋለን" ሲሉ ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ላወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም ታማኝ ሆኖ መቆየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ አመልክቶ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን በህወሓት እየተፈጸመ ነው ላለው ጭፍጨፋ የሚያሳየውን ቸልተኝነት እንዲያቆም ጥሪ አቅርቧል።
ጨምሮም ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ቡድኑ አዳዲስ ጥቃቶችን በአጎራባች ክልሎች ላይ በመክፈት የነዋሪውን ሕይወት እንዲያናጋ አይፈቅድም ብሏል።
የፈደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የተለያየ ጥረት ማድረጉን ያመለከተው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ህወሓት ግን አዲስ ጥቃቶችን በመክፈት ግጭቱን ወደ አጎራባች ክልሎች በማስፋት አገሪቱን የማናጋት እርምጃ እየወሰደ ነው ብሏል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ለስምንት ወራት የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት ከአንድ ወር በፊት የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ያስወጣ ቢሆንም የህወሓት ኃይሎች የጥቃት አድማሳቸውን ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልል በማስፋት የተለያዩ ቦታዎችን መያዛቸው ይታወሳል።
መንግሥት በተናጠል ባወጀው የተኩስ አቁም ምክንያት ያሳየው ትዕግስት በህወሓት እርምጃ ምክንያት እየተፈተነ በመሆኑ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ለመውሰድ ሊገደድ እንደሚችል ያሳወቀው የህወሓት ኃይሎች ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ ነው።
የህወሓት አማጺያን በአፋርና በአማራ ክልሎች ውስጥ እየፈጸሙት ያለውን ጥቃት እንዲያቆሙና ከክልሎቹ እንዲወጡ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ቢጠይቁም የቡድኑ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል አለ ያሉት "የእንቅስቃሴ መዘጋት አስካልተነሳ" ድረስ ጥያቄውን እንደማይቀበሉ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ገልጸዋል።
አማጺያኑ ጥቃት ከሰነዘሩባቸውና ከተቆጣጠሯቸው የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከ200 ሺህ በላይ እንዲሁም በአፋር ክልል ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ የክልሎቹ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
የህወሓት ኃይሎች አመራር ናቸው የሚባሉት ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ከቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በኩል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየሰነዘሩ ያሉት የተኩስ አቁም ለማድረግ ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች የፌደራሉ መንግሥት እንዲቀበል ጫና ለማሳደር መሆኑን ተናግረው ነበር።
በአገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ኃይሎችን ጥቃት ለመመከት የአማራና የአፋር ክልሎች ለሕዝባቸው የክተት ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ሌሎችም የአገሪቱ ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን ወደ ጦርነቱ አካባቢ ልከዋል።














