ቀይ መስቀል በትግራይ የሚገኙ ምርኮኞችን መጎብኘት ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር (አይሲአርሲ) በትግራይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች አባላትን መጎብኘት መጀመሩን አስታወቀ።
ማሕበሩ ትናንት አመሻሽ ባወጣው መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር ኦፕሬሽን ኃላፊ ማሪያ ሶሌዳድ ሩኤዳ ጋርሺያ "በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን መጎብኘት ከዋና ኃላፊነቶቻችን መካከል የሚገኝ ሲሆን በአገሪቱም ማሕበሩ ከተቋቋመበት ምክንያት አንዱ ነው። ይህን ቁልፍ እንቅስቃሴ በትግራይ መጀመራችን ደስተኞች ነን" ብለዋል።
ማሕበሩ በትግራይ ክልል በእስር ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች አባላትን በተጠናቀቀው ሳምንት መጀመሪያ መጎብኘት ጀመርኩ ከማለት ውጪ የጦር ኃይል አባላቱን ብዛት እና የሚገኙበትን ሁኔታ ግልጽ አላደረገም።
የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የመከላከያ ሠራዊት መቀለን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ መዲና ከተመለሱ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን መማረካቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
በትግራይ ኃይሎች የተማረኩ የአገር መከላከያ አባላት ናቸው የተባሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሠራዊት አባላት በኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ላይ በመቀለ ጎዳናዎች ላይ መታየታቸው ይታወሳል።
ከቀናት በፊት የህወሓት አመራሮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል በቁጥጥር ሥር ካዋሏቸው እስረኞች መካከል 1ሺህ የሚሆኑ እስረኞችን ስለመልቀቃቸው ተናግረዋል። ይህ ግን በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።
ከወራት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዳደረሰ ቢነገርም አስካሁን ከየትኛውም ወገን ይህ ነው የሚባል ዝርዝር መረጃ አልወጣም።
ለስምንት ወራት የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት የፌደራል መንግሥቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል።
አማጺው ኃይል በበኩሉ በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ለማድረግ ሰባት ነጥቦችን የያዘ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርቧል።

ማሕበሩ በመላው ዓለም በእስር የሚገኙ ሰዎችን በተደጋጋሚ በመጎብኘት፣ ከእስሮች ጋር በመነጋገር ሰብዓዊ አያያዝ እየተደረገላቸው እንደሆነ የማረጋገጥ እና ማሻሻያዎች እንዲደረጉ እሰራለሁ ብሏል።
ማሕበሩ በመሰል ሥራዎቹ የሚያገኛቸው ግኝቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሚስጥር ውይይት ይደረግበታል ብሏል።
እአአ 2020 ላይ በመላው አገሪቱ በሚገኙ 50 እስር ቤቶች ተዟዙሮ ወደ 72ሺህ የሚጠጉ እስረኞችን መጎብኘቱን ማሕበሩ የገለጸ ሲሆን ለእስረኞችም መሠረታዊ ቁሶች እንዲሁም የውሃ እና መጸዳጃ ቤት አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጿል።
በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሲለግስ መቆየቱን እና በእስር ላይ ሆነው ከቤተሰብ አባላታቸው ጋር የተለያዩ መልሰው እንዲገናኙ ሚናውን መወጣቱን በትናንት መግለጫ አስነብቧል።
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በትግራይ የመሠረታዊ ሸቀጦች እና የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ማስታወቁ ይታወሳል።
ማሕበሩ ሐምሌ 8 ባወጣው መግለጫ በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የምግብ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፤ በመላው ትግራይ ባንኮች ዝግ በመሆናቸው ሰዎች መሠረታዊ ግብይቶችን ለመፈጸም የጥሬ ገንዘብ እጥረት አጋጥሟቸዋል ብሎ ነበር።














