ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካው ሁከት የኢትዮጵያውያን ንብረት መዘረፉ ተነገረ
የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማን እስር ተከትሎ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው የተቃውሞ ሰልፍና ነውጥ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ንብረታቸው መዘረፉን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ግርማ ፊጣ እንፈገለጹት የእሳቸውን ጨምሮ የበርካታ ኢትዮያዊያን ሱቆች ተዘርፈዋል።
ዛሬ ማክሰኞ የአገሪቱ ፖሊስ እንዳስታወቀው በሁከቱ ቢያንስ የ30 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 800 ያህል ሰዎች ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ለተቃውሞ የወጡት ሰዎች በተለያዩ ከተሞች ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት ንበረቶች በእሳት ወድመዋል፣ ዘረፋ ተፈጽሟል አውራ ጎዳናዎች ተዘግተዋል።
የይህንንም ተከትሎ አመጸኞቹን ለመቆጣጠር ከአቅሙ በላይ የሆነበትን የአገሪቱን ፖሊስ ለማገዝ ጦር ሠራዊቱ እንዲሰማራ ተደርጓል።
በደቡብ አፍሪካ ምን ተፈጠረ?
የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማን እስር ተከትሎ በመላው አገሪቱ ተቃውሞና ሁከት የተቀሰቀሰው ባለፈው ሳምንት ማብቂኣ ላይ ነው።
ጃኮብ ዙማ ከቀናት በፊት እጃቸውን ለፖሊስ ከሰጡ በኋላ የቀድሞው ፕሬዝደንት ደጋፊ የሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት ነበር ወደ ጎዳናዎች የወጡት።
ፖሊስ እንደሚለው በጃኮብ ዙማ የትውልድ ቦታ ክዋዙሉ-ናታል ተቀስቅሶ በመላው አገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣውን አለመረጋገት ወንጀለኛ ቡድኖች መጠቀሚያ እያደረጉት ነው።
ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች ፖሊስ ምላሽ እየሰጠ ሲሆን እስካሁን ድረስ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም ይፋ አድርጓል።
ከትናንት በስቲያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች ዱላ እና ፍልጥ ይዘው በጆሃንስበርግ ከተማ መሃል ታይተዋል።
ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች የጆሃንስበርግን ዋና ጎዳናን ዘግተው ነበር። በተቃውሞው ሕንጻዎች እና መኪኖች በእሳት ወድመዋል።
ዝርፊያ
አቶ ግርማ ፊጣ ከ17 ዓመታት በላይ በደቡብ አፍሪካ እንደኖሩ ይናገራሉ። መኖሪያቸውንም በጃኮብ ዙማ የትውልድ ስፍራ ክዋዙሉ-ናታል ዋና ከተማ ፒትመርስበርግ አድረገዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ መሪ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ግርማ የአሁኑ ችግር ቀደም ሲል በደቡብ አፍሪካ ሲከሰት ከነበረው የመጤ ጠል (ዜኖፎቢያ) እንቅስቃሴ የሚበልጥ መሆኑን ይናገራሉ።
ቀደም ሲል መጤ በሚባሉት የውጭ አገራት ዜጎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እና ዝርፊያ በዚህኛው ግን ሁሉንም ያማከለ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
"ሁሉንም ነገር ነው የዘረፉት" የሚሉት አቶ ግርማ "አሁን ለህይወታችን እየሰጋን ነው" ይላሉ።
እስካሁን በአካባቢያቸው ዘርፊያዎች ማጋጠማቸውን ነገር ግን በህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ገልጸዋል።
ጥበቃ ከሚያከናውኑ ሰዎች በመክፈል አካባቢያቸውን ከዘራፈዎች ለማስተበቅ ቢሞክሩም ምክንያቱ ሳይገለጽላቸው የጥበቃ ሰዎቹ ቦታውን ለቀው ሄደዋል ብለዋል።
በአካባቢው ያሉ የንግድ ሱቆችን ጨምሮ የነዳጅ ማደያዎች በመዘጋታቸው ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ እንደሌለ ጠቅሰዋል።
"የእኔ ሦስት ሱቅ ተዘርፏል" ሚሉት አቶ ግርማ "አንደኛው ሱቅ 1.8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንበረት የነበረው ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ እያንዳንዳቸው 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው" መሆኑንና በተቃዋሚዎቹ መዘረፈፋቸውን ጠቅሰዋል።
ከከተማው ዳርቻ ያሏቸውን ሱቆች ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ "ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው" ያሉት ሲሆን ቤተሰብ የሚተዳደርበት እና ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሌላኛውን በከተማ መሐል ሚገኘው ሱቃቸውን ከዝርፊያ ለመጠበቅ እየሞከሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
ምንም ልዩነት ሳይደረግ በአካባቢው ከ160 በላይ ሱቆች መዘረፋቸውን የጠቀሱት አቶ ግርማ ትልልቅ ሱቆች እና የገበያ ማዕከሎች ሌሎችም ቃጠሎ የደረሰባቸው መሆኑን አመልክተው እስካሁንም ጭሱ በአካበቢው እንደሚታይ ተናግዋል።
እንቅስቃሴዋ የተገታው ጆሃንስበርግ
ጆሃንስበርግ ውስጥ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ወ/ሮ መዓዛ ተስፋዬ እንደተናገሩት ረብሻው መቀስቀሱን ተከትሎ በጣም አሳሳቢ እና አስፈሪ ሁኔታ ተከስቷል ብለዋል።
ወደ ውጭ ባይወጡም ከሰዎች እንቅስቃሴ በስተቀር ሱቆች እና የንግድ ተቋማት አሁንም ዝግ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከጆሃንሰበርግ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች አሁንም ዝርፊያ መኖሩን ጠቅሰው ቃጠሎ መኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።
"ያለው ሁኔታ ደስ አይልም። እኛ ጋር [ጆሃንሰበርግ] እሁድ በጣም አስከፊ ነበር። ኢትዮጵያዊያን እና ማሊያዊንን ጨምሮ ስደተኛው በድንጋይም በዱላም መክተዋቸዋል" ብለዋል።
አካባቢው በዚህ መልኩ ውጥረት ከነገሰበት በኋላ ፖሊሶች ምሽት 12፡00 ሰዓት ገደማ መድረሳቸውን ተከትሎ አካባቢያው አንጻራዊ ሰላም እንደሰፈነበት ተናግረዋል።
በሌሎች አካባቢዎች ግን ችግሩ መቀጠሉንና ምንም አይነት የተረጋጋ መንፈስ እንደማይታይና ሱቆች ዝግ ሆነው እንዳሉ ጠቁመዋል።
ወ/ሮ መዓዛ በሚኖሩበት አካባቢ ዝርፊያ እና ቃጠሎ ባይኖርም "የመጡት ለመዝረፍ እና ለማቃጠል ነበር። ግን መልሰዋቸዋል" ብለዋል።
በከተማዋ የሰዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም "ከአሁን ከአሁን መጡ በሚል ስጋት ቤት ቁጭ ብለናል። ቤት ሆነን የንግድ ተቋማት እስኪከፈቱ እየጠበቅን ነው" ሲሉ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
የመንግሥት እርምጃ
ደቡብ አፍሪካ የተነሳውን ሁከት ለመቆጣጠር ሠራዊቷን አሰማርታለች።
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ እስርን ተከትሎ በአገሪቱ ለተፈጠረው አመጽ ምላሽ ለመስጠት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ "ሕዝቡ አመጹን እንዲቃወም" ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው ሳምንት ዙማ እጃቸው ለፖሊስ ከሰጡ በኋላ ቢያንስ ሰላሳ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ወደ 800 የሚጠጉት ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በጋውቴንግ ግዛት እና በዙማ የትውልድ ስፍራ በክዋዙሉ-ናታል የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አባላት ተሰማርተው ሁከቱን ለመቆጣጠር እየጣሩ ነው።
የፖሊስ ሚኒስትሩ ሔኪ ቼሌ ዛሬ እንደተናገሩት የሚፈጸመው ዘረፋ እንደቀጠለ ሲሆን እንቅስቃሴ በመቋረጡ ምክንያት ነዋሪዎች መሠረታዊ ሸቀጦች ለማግኘት ችግር ገጥሟቸዋል ብለዋል።
26 ሰዎች በተገደሉባት በኩዋዙሉ ናታል ክፍለ ግዛት ውስጥ እንዲሁም ሁከቱ በበረታባት ጉአቴንግ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ አስፈላጊ እንዳልሆነ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ተናግረዋል።
በሥልጣን ዘመናቸው ስለተፈጸመ የሙስና ድርጊት ለሚደረግ ምርመራ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠርተው ባለመገኘታቸው ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ በተባሉት ጃኮብ ዙማ ምክንያት ነው ሁከቱ የተቀሰቀሰው።
በሙስና ውስጥ እጃቸው እንደሌለ የሚያስተባብሉት ዙማ የ15 ወራት እስር ተፈርዶባቸው ባለፈው ረቡዕ እጃቸውን ለፖሊስ ሰጥተዋል።