ኮሮናቫይረስ፡ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ የሚያስፈልገው የኮቪድ የይለፍ ወረቀት ምን ይጠይቃል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ ሕብረት የዲጂታል የኮቪድ-19 የምስክር ወረቀት ወይም የክትባት ፓስፖርት በሁሉም 27 አባል አገራቱ እየተሠራጨ ነው።
ዲጂታል የኮቪድ-19 የምስክር ወረቀት በአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት የሚኖሩ ሕዝቦች የኮቪድ-19 ክትባት መውሰዳቸውን፣ በቅርቡ የፒሲአር ምርመራ ምርመራ አድርገው ከኮቪድ ነጻ መሆናቸውን እና ከበሽታው ማገገማቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።
ይህ የምስክር ወረቀት በሁሉም 27 አባል አገራቱ የሚገኝ ሲሆን ተቀባይነትም አግኝቷል። በተጨማሪም ስዊትዘርላንድ፣ አይስላንድ፣ ኖርዌይ እና ሌሽተንስታይን ተቀብለውታል።
አገልግሎቱም ነጻ ነው የሚሰጠው።
በመሆኑም ሁሉም የሕብረቱ አባል አገራት ዜጎች እንዲሁም ሌሎች በአገራቱ በሕጋዊ መንገድ የሚቆዩ፣ የሚኖሩ ወይም ወደ ሌሎች አባል አገራት ለመጓዝ መብት ያላቸው መተግበሪያውን አውርደው የምስክር ወረቀቱን ማግኘት ይችላሉ።
አንዳንድ አገራት በፈቃደኝነት የምስክር ወረቀቱን ቀደም ብለው እየተጠቀሙበት ቢሆንም በይፋ የተዋወቀው ግን ሐሙስ ዕለት ነው።
ፓስፖርቱ በዲጂታል አማካይነት በአፋጣኝ የአንድን ግለሰብ የክትባት መረጃ ይሰጣል።
የምስክር ወረቀቱ በአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ለሚጓዙ መንገደኞች ቀላል አሰራር ነው የሚል ተስፋ ተጥሎባታል።
ይሁን እንጅ የምስክር ወረቀቱ ብቸኛ የጉዞ መረጃ አይደለም። መንገደኞች ፓስፖርታቸውን እና ሌሎች መታወቂያቸውን መያዝ ይጠበቅባቸዋል። የምስክር ወረቀቱን የያዘ ሰው ግን ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ሲያቋርጥ ወይም ወደ ሌላ አገር ሲጓዝ ምርመራ ማካሄድ ወይም ለይቶ ማቆያ መግባት አይጠበቅበትም።
ይህ በዩኬ ካለው የኮቪድ የይለፍ ወረቀት ጋር ተመሳሳይ ነው?
የአውሮፓ ሕብረት የኮቪድ-19 የይለፍ የምስክር ወረቀት ከዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ጋር ተመሳሳይ አይደለም፤ ነገር ግን ሁሉም የሚያሳዩት ተመሳሳይ መረጃዎችን ነው። ዓላማውም በቀላሉ የአንድን ሰው የኮቪድ ጤንነት ሁኔታን ማወቅ ነው።
በዲጂታል የኤንኤችኤስ ኮቪድ የይለፍ ወረቀትን በኤንኤችኤስ መተግበሪያ አማካይነት ማግኘት ይቻላል።
መተግበሪያው በኢንግላንድ ዕድሜያቸው ከ16 በላይ ለሆኑት መከተባቸውን፣ ባለፉት 48 ሰዓታት የፒሲአር ምርመራቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን እና ከኮቪድ 19 ማገገማቸውን ያሳያል።
ሁለት ጊዜ ክትባቱን ለመውሰድ የወረቀት ማረጋገጫ ለማግኘትም በኦንላይን ወይም 119 ላይ በመደወል መጠየቅ ይቻላል።
በስኮትላንድ፣ በዌልስ እና ከሐምሌ ወር መጀመሪያ እስከ አጋማሹ ድረስ በሰሜን አየርላንድ የሚገኙ ሰዎች የወረቀት የምስክር ወረቀቱን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
የአውሮፓ ሕብረት የዩናይትድ ኪንግደምን የኮቪድ ይለፍ ወረቀት ይቀበላል?
አይቀበልም። ነገር ግን እንደ ግሪክ እና ስፔን ያሉ አገራት እየተቀበሉ ነው።
የአውሮፓ ሕብረት የዲጂታል የምስክር ወረቀቱ ከአባል አገራቱ ውጭ ላሉ አገራት ተስማሚ መሆኑን ለማረጋገጥ እየሰራሁ ነው ብሏል።
የሌሎቹ አገራት የምስክር ወረቀት የአውሮፓ ሕብረትን ደረጃና ሥርዓት ያሟላ ከሆነ በሁሉም አገራቱ ተቀባይነት እንዲኖረው መወሰን ይቻላል ብሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ነጻ እና ግልጽ የሆነ ጉዞ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብሏል።
የይለፍ ወረቀቱ በተወሰደው የክትባት ዓይነት ይወሰን ይሆን?
በዩናይትድ ኪንግደም ተቀባይነት ያገኙት አራት ክትባቶች በአውሮፓ ሕብረትም ተቀባይነት አግኝተዋል። ይሁን እንጅ ሦስቱ ክትባቶች የሚታወቁት በተለያየ መለያ (ብራንድ) ነው።
ለምሳሌ
• የፋይዘር- ባዮንቴክ ክትባት ኮሚርናቲይ በመባል ይታወቃል።
• የኦክስፎርዱ አስትራዜኒካም ቫክስዜቭሪያ ይባላል።
• ሞደርና ክትባትም ስፓይክቫክስ በመባል ይጠራል።
• ጃንሰን ደግሞ አንዳንዴ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በመባል ይታወቃል።
ሆኖም በሕንዱ ሴረም ተቋም የተመረተው የአስትራዜኔካ ክትባት ኮቪሼልድ በሚል ሦስተኛ ስም ይጠራል።
ምንም እንኳን ኮቪሼልድ በአውሮፓ ከተመረቱት ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም የአውሮፓ ሕብረት ጥቅም ላይ እንዲውል አልፈቀደም።
ኮቪሼልድ በኮቫክስ የክትባት ፕሮግራም አማካይነት በአብዛኛው ጥቅም ላይ የዋለው በድሃ አገራት ነው። በመሆኑም የአውሮፓ ሕብረት ፓስፖርት ከእነዚህ አገራት የሚሄዱ መንገደኞችን ያገላል የሚል ስጋት አለ።
የአውሮፓ የመድኃኒት ኤጀንሲም በሕንድ የሚገኘውን የአስታራዜኒካ ክትባት ማምረቻ ቦታ መጎብኘት አይጠበቅበትም።
ምክንያቱም ሕብረቱ ከዚያ ምንም ክትባት እየተቀበለ ስላይደለ ነው። ነገር ግን የሕንዱ ሴረም ተቋም ኮቪሼልድ በአውሮፓ ሕብረት በአስቸኳይ ተቀባይነት እንዲያገኝ መጠየቅ እንዳለበት ተረድቷል።
አስታራዜኒካ በበኩሉ ኮቪሼልድ ክትባት ለኮቪድ የይለፍ ወረቀት ተቀባይነት እንዲያገኝ ከኤጀንሲው ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል።
ነገር ግን ኤጀንሲው አሁን ላይ ለገበያ ማረጋገጫ ጥያቄ እንደማይቀበል አስታውቋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ግን የኮቪሼልድን ክትባት አስትራዜኔካ በሚል ከተከተቡ ተቀባይነት አለው።
አብዛኞቹ የዩናይትድ ኪንግደም አስትራዜኒካ ክትባት የገቡት ከሰሜን ዌልስና ስታፎርድሻየር ሲሆን 5 ሚሊየን ኮቪሼልድ የሚል መለያ ያላቸው ክትባቶች የገቡት ግን ከሕንድ ነው።
የአገሪቷ የጤና መሥሪያ ቤት በግለሰቦች የክትባት አቅርቦት ላይ ከንግድና የደህንነት ጉዳይ ጋር በተያያዘ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልግ ገልጿል።
አፍሪካስ?
የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የአውሮፓ ሕብረት ውሳኔ ሳይንስና መረጃዎች ላይ የተመሰረተ አይደለም ብሏል።
የማዕከሉ ዳይሬክተር ጆን ኬንጋሶንግ በሕንድ የተመረተው ክትባት የአውሮፓ ሕብረት ከተጠቀመው ክትባት ጥራቱ ዝቅተኛ ነው የሚል ማረጋገጫ ባለመኖሩ ውሳኔው ሳይንሳዊ አይደለም ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ዳሬክተሩ የአውሮፓ ሕብረት አፍሪካ ወረርሽኙን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት ለማንኳሰስ ከሚጠቀምበት ፖሊሲ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣናት ጉዳዩን ለመፍታት ከአውሮፓ ሕብረት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።
ነገረ ግን ገለልተኛ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት አሁንም ቢሆን በዓለም ጤና ድርጅት የተረጋገጡ እንደ ኮቪሼልድ እና በሕንድ የተመረተውን የአስትራዜኒካ ክትባቶችን መቀበል ይችላሉ።
ስምንት የአውሮፓ አገራት ኮቪሼልድን ለይለፍ ለመጠቀም መፍቀዳቸው ተገልጿል። ከእነዚህ አገራት መካከል ኢስቶኒያ፣ ኦስትሪያ፣ ጀርመን፣ ስሎቬኒያ፣ ግሪክ፣ አይስላንድ፣ አየርላንድ እና ስፔን ይገኙበታል።















