እነጀነራል ሰዓረ መኮንን የገደለው ጠባቂያቸው የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈረደበት

አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ

የፎቶው ባለመብት, ETV

የምስሉ መግለጫ, አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ባልደረባቸውን የገደለው ጠባቂያቸው የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ ባሳለፈው ውሳኔ ወንጀሉን ፈጽሟል ባለው የጀነራሉ ጠባቂ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ላይ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት በይኗል።

የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ባልደረባቸውን ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ወንጀሉን የፈጸመው።

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ሦስትኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት አስር አለቃ መሳፍንትን በጀነራል ሰዓረ መኮንን እና በጓደኛቸው ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሲል ግንቦት 27/2013 ውሳኔውን አሳልፎ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ግለሰቡ ለፈጸመው ወንጀል በሞት እንዲቀጣ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቀረበውን የቅጣት ማቅለያ ከተመለከተ በኋላ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ በጀነራል ሰዓረ መኮንን መኖሪያ ቤት ውስጥ ግድያውን በመፈጸም የተከሰሰው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ጉዳይን የተመለከተው ችሎት ተከሳሹ የሰፊ የወንጀል ድርጊት አካል ሆኖ ወንጀሉን መፈጸሙን አመልክቶ ነበር።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መረጃ መሰረት የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተላለፈበት ተከሳሹ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በአማራ ክልል የቀድሞ የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ በነበሩት በብርጋዲየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ በተመራ ሰፊ ከባድ የወንጀል ድርጊቶች ሴራ ውስጥ ተሳታፊ እንደነበር ተገልጾ ነበር።

በዚህም ተከሳሹ በዚሁ ሴራ ውስጥ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጀነራል ሰዓረ መኮንን እንዲገድል እንዲሁም ሌላ ግለሰብ ደግሞ ምክትል ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጀነራል ብርሃኑ ጁላን እንዲገድል ተልዕኮ ሰጥቷቸው እንደነበር ተገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለውም ግንቦት 15/2011 ዓ.ም ምሽት ሦስት ሰዓት ላይ አስር አለቃ መሳፍንት ባሕር ዳር ከተማ የተፈፀመውን ጥቃት ሲሰማ "ተኩሶ ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራን በመግደል ለማምለጥ ሲሞክር ተከቦ በቁጥጥር ስር ውሎ" ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱን ገልጿል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ሦስትኛ የጸረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በክሱ ላይ የቀረበውን የግራ ቀኝ ክርክርና ማስረጃ ከመዘነ በኋላ ነበር ተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ በመስጠት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ከሰማ በኋላ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወሰነው።

ሰኔ 15/2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የተገደሉት ኤታማዦር ሹሙ፤ ለረጅም ዓመታት በኃላፊነቱ ላይ የቆዩትን ጄነራል ሳሞራ የኑስን ተክተው የአገሪቱ ሠራዊት አዛዥ ከሆኑ ብዙም አልቆዩም ነበር።

በጥቃቱ ወቅት በአጋጣሚ በጄነራሉ ቤት የተገኙት ጓደኛቸውና የቀድሞ የሠራዊቱ አባል ጀነራል ገዛኢ አበራም በተፈጸመባቸው ጥቃት ተገድለዋል።

ዐቃቤ ሕግ የዚሁ ሴራ አካል ነው ባለው ድርጊት በዚያው ዕለት ምሽት ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ በባሕር ዳር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩትን ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮቻቸው ላይ ግድያ መፈጸሙ ይታወሳል።

የእድሜ ልክ ጽኑ አስራት የተፈረደበት አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ከቆሰላ በኋላ ስለነበረ ለረጅም ጊዜ በህክምና ላይ ቆይቷል።