ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ አፍሪካ ጠንከር ያሉ አዳዲስ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ገደቦችን ይፋ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአገራቸው ሊከሰት የሚችለውን ሦስተኛውን ዙር የኮሮናቫይረስ ማዕበል ጉዳት ለመቆታጠር ጠንከር ያሉ አዳዲስ ገደቦችን ይፋ አደረጉ።
በዚህም ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የአልኮል ሽያጭን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እና የሐይማኖት ስብሰባዎች ክልከላ ተጥሎባቸዋል።
በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የማታ የሰዓት እላፊ ጊዜን ሲያራዝም በሚቀጥለው ሳምንት ትምህርት ቤቶችም ዝግ ይሆናሉ።
በሕንድ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው 'ዴልታ' የተሰኘው የኮሮናቫይረስ ዝርያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ ነው። አገሪቱን በጥር ወር ወደነበረችበት ጥብቅ ክልከላ ከመመለሷ በተጨማሪ ባለፈ ቅዳሜ ብቻ ከ18,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተመዝግቧል።
ፕሬዝዳንት ሲረል ራማፎሳ እየተተገበሩ ያሉት እርምጃዎች የቫይረሱን የስርጭት ፍጥነት እና መጠን ለመቋቋም በቂ አይደሉም ብለዋል።
"በሁሉም መመዘኛዎች ከቀደሞዎቹ የከፋ በሚመስል አውዳሚ ማዕበል ውስጥ ነን። የሦስተኛው ማዕበል ጫና ከቀደሙት ሁለቱ ከፍ ያለ ይመስላል።"
የሕዝብ ጤና ተቋማት አቅማቸውን አሟጠው እየሠሩ በመሆናቸው እና የግል ሆስፒታሎችም ችግር ውስጥ በመገኘታቸው አገሪቱ ከባድ ፈተና እየገጠማት መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ አፍሪካ የክትባት ዘመቻ አዝጋሚ ሆኖ እየተጓዘ ነው። ከ59 ሚሊዮን ሕዝቧ ውስጥ እስካሁን የተከተቡት 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ናቸው።
ራማፎሳ እንደሚሉት አዲስ የሚመጡ ክትባቶች ፕሮግራሙ እንዲፋጠን ያስችላሉ ብለዋል።












