የቤት ሠራተኛዋን አሰቃይታ የገደለችው አሰሪ የ30 ዓመት እስር ተፈረደባት

የምያንማር ዜግነት ያላትን የቤት ሠራተኛዋን አስርባለች፣ አሰቃይታለች እንዲሁም ገድላለች የተባለችው ሴንጋፖራዊት ጥፋተኛ ተብላ የ30 ዓመት አስር ተፈረደባት።

ፒያንግ ንግያህ ዶን የተባለችው ምያንማራዊት የቤት ሠራተኛ ከአራት ዓመት በፊት በደረሰባት ጉዳት ህይወቷ ሲያልፍ ክብደቷ 24 ኪሎ ግራም ነበር ተብሏል።

የሟቿ የቤት ሠራተኛ ቀጣሪ የሆነችው ጊያቲሪ ሙሩጋያን የፈጸመችውን ግፍ ክሷን ሲከታተል ነበረው ዐቃቤ ሕግ "ፍጹም ከሰብአዊነት የራቀ እና በክፋት የተሞላ" ብሎታል።

ይህ በሠራተኛዋ ላይ የተፈጸመው ግፍ አስካሁን በሀብታሟ አገር ሴንጋፖር ውስጥ ከተፈጸሙትና ትኩረትን ከሳቡ አስከፊ ድርጊቶች ሁሉ የባሰው ነው ተብሏል።

የ40 ዓመቷ አሰሪ የነፍስ ማጥፋትን ጨምሮ የቀረቡባትን በርካታ ወንጀሎችን መፈጸሟን አምናለች።

ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛም ዐቃቤ ሕግ በ24 ዓመቷ የቤት ሠራተኛ ላይ የተፈጸመው ሰቆቃ፣ ማዋረድ፣ ማስራብና በመጨረሻም ግድያን በጣም በሚያስደነግጥ ሁኔታ ለችሎቱ አስረድቷል ብለዋል።

በወጣቷ የቤት ሠራተኛ ላይ አሰሪዋ አሰቃቂውን ድርጊት መፈጸም የጀመረችው ልጅቷ ሥራ ፍለጋ ወደ እርሷ ቤት ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ተከሳሽ ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።

በቤቱ ውስጥ ከሚገኝ የደኅንነት ካሜራ የተገኙ ምስሎች ሠራተኛዋ በህይወት የነበረችበትን የመጨረሻ የስቃይ ወቅትን ያሳየ ሲሆን፤ አሰሪዋ በየቀኑ በተደጋጋሚ ትደበድባት እንደነበር ቪዲዮው ላይ ታይቷል።

በፍርድ ቤቱ እንደተነገረውም የቤት ሠራተኛዋ በቂ ምግብ የማይሰጣት ሲሆን የምትመገበውም በውሃ የራሰ ቁራሽ ዳቦ፣ ከፍሪጅ የወጣ ቀዝቃዛ ምግብ ወይም ትንሽዬ ሩዝ ነበር።

በዚህ ምክንያት የቤት ሠራተኛዋ በአሰሪዋ ቤት ውስጥ በቆየችባቸው 14 ወራት ውስጥ 15 ኪሎ ቀንሳ ነበር ተብሏል።

ወጣቷ የቤት ሠራተኛ ከአራት ዓመት በፊት ለረጅም ሰዓት በተፈጸመባት ተደጋጋሚ ድብደባ ነበር ህይወቷ ያለፈው።

ከሞተች በኋላ የተደረገው የአስከሬን ምርመራ ሪፖርት እንዳመለከተው ወጣቷ በተደጋጋሚ አንገቷን በመታነቋ ምክንያት ወደ አንጎሏ በቂ ኦክስጂን ሳይደርስ በመቅረቱ ነው ለሞት የበቃችው።

የተከሳሿ ጠበቃ ደንበኛው የተለያዩ ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ስላሉበት ለፈጸመችው ወንጀል ከዘጠኝ ዓመት ያልበለጠ እስር እንድትቀጣ ጠይቆ ነበር።

ከግለሰቧ በተጨማሪ የፖሊስ መኮንን የሆነውና አሁን ከሥራው የታገደው ባለቤቷ እንዲሁም የተከሳሿ እናት ከግድያው ጋር በተያያዘ በርካታ ክሶች እንደቀረበባቸው ተዘግቧል።

ሴንጋፖር ውስጥ አብዛኞቹ ከኢንዶኔዢያ፣ ከምያንማር እና ከፊሊፒንስ የመጡ 250 ሺህ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ሠራተኞች ይገኛሉ።

በአገሪቱ በቤት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸም በደል ያልተለመደ አይደለም፤ ከሁለት ዓመት በፊት ሌሎች ባልና ሚስት በቤት ሠራተኛቸው ላይ በፈጸሙት በደል የተነሳ ለእስር ተዳርገዋል።