ኮሮናቫይረስ፡ ድሃ ሃገራት ክትባት እያለቀባቸው ነው- የዓለም ጤና ድርጅት

በዓለም አቀፍ የክትባት የመጋራት መርሃግብር አማካይነት የኮቪድ -19 ክትባቶችን የሚያገኙ ብዙ ድሃ ሃገሮች ለመከተብ የሚያስችል በቂ መጠን የላቸውም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ አማካሪው ዶ/ር ብሩስ አይልወርድ በኮቫክስ መርሃ ግብር 90 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ለ 131 ሃገራት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ይህ ግን በዓለም ዙሪያ እየተዛመተ ከሚገኘው ቫይረስ ህዝቦችን ለመከላከል በቂ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

እጥረቶቹ የተከሰቱት በአንዳንድ የአፍሪካ ሃገሮች ሦስተኛ ዙር ማዕበል መከሰቱን ተከትሎ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በሃገራቸውን እየጨመረ የመጣውን ቫይረስ ለመከላከል እየሠራች ባለችበት ወቅት ሃብታም ሃገራት ክትባት ማከማቸታቸውን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአህጉር ደረጃ አፍሪካ ውስጥ 40 ሚሊዮን ዶዞች (መጠን) ብቻ መሰጠቱ ከአጠቃላዩ ህዝብ ከ2 በመቶ በታች እንዲደርሰው ምክንያት መሆኑን ራማፎሳ ገልጸዋል፡፡

ይህንን ለመቅረፍ በደቡብ አፍሪካ ተጨማሪ ክትባቶችን ለማምረት የሚያስችል ማዕከል ለመክፈት መንግስታቸው ከኮቫክስ ጋር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮቫክስ ባለፈው ዓመት የኮቪድ-19 ክትባት በዓለም ዙሪያ እንዲቀርብ ለማድረግ የበለጸጉ አገራት ለድሃ አገራት ወጪዎችን ድጎማ በማድረግ የተቋቋመ ነው፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚመራው ኮቫክስ እአአ በ 2021 መጨረሻ በዓለም ዙሪያ ሁለት ቢሊዮን ክትባቶችን ለማቅረብ ግብ አንግቦ ነበር፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ለድሃ አገራት በመስጠት ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነውን ህዝብ ለመከላከል የሚረዳ በቂ ክትባቶችን ለማሰራጨት ተስፋ አቅዶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የክትባቶቹ ስርጭት በምርት መዘግየት እና በአቅርቦት መቆራረጥ ተስተጓጉሏል። በዚህም በኮቫክስ ላይ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ባደረጉ ሀገሮች እጥረት አስከትሏል፡፡

በቅርቡ ክትባቶች እንዳለቀባቸው ሪፖርት ካደረጉ ሃገራት መካከል ኡጋንዳ፣ ዚምባብዌ፣ ባንግላዲሽ እና ትሪኒዳድ እና ቶባጎ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ሰኞ በጄኔቫ የዓለም ጤና ድርጅት መግለጫ ላይ ዶ/ር አይልወርድ መጠነ ሰፊ እጥረቶች መኖራቸውን አምነዋል፡፡

በኮቫክስ ከተሳተፉት 80 ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ውስጥ "ቢያንስ ግማሾቹ ፕሮግራማቸውን ለማስቀጠል የሚያስችል በቂ ክትባት የላቸውም" ብለዋል ዶ/ር አይልወርድ፡፡

"በየቀኑ ከሃገራት የምንሰማውን ከተመለከትን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሃገሮች እጥረት አለባቸው። ተጨማሪ ክትባት ለማግኘትም ጥሪ እያቀረቡ ነው፡፡ እውነታው ግን ምናልባትም ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችላል፡፡" .

አንዳንድ አገራት እጥረቶችን ለመቋቋም አማራጭ መንገዶችን እንደሞከሩ ገልጸው ለክትባቶች ከገበያ ዋጋ በላይ መክፈላቸውን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

የክትባት አቅርቦቶች ጫና ውስጥ በመግባታቸው ትርፍ ክትባት ያላቸው አንዳንድ ሃብታም ሀገሮች በኮቫክስ እና በሌሎችም መንገዶች ልገሳን ለማሳደግ ጥረቶችን እያደረጉ ናቸው፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሰኞ ዕለት 55 ሚሊዮን ክትባቶችን ለተቸገሩ ሃገሮች ለመስጠት እንዴት እንዳቀደ አስታወቋል፡፡

41 ሚሊዮን የሚሆኑትን በኮቫክስ በኩል ሲያሰራጭ 14 ሚሊዮኑ ደግሞ ቅድሚያ ያስፈልጋቸው ተብለው ለሚታመኑ ሃገራት ይከፋፈላል፡፡

እነዚህ ክትባቶች አሜሪካ በኮቫክስ በኩል 500 ሚሊዮን ዶዝ ለመለገስ ያቀደችው ውስጥ አይካተቱም፡፡ ፕሬዝዳንት ባይደን ይህን ቃል የገቡት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ነው፡፡

በስብሰባው የቡድን ሰባት ሃገራት በዚህ የፈረንጆች ዓመት አንድ ቢሊዮን ክትባቶችን ለድሃ አገራት ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡

ህልም የሌለው፣ በጣም ቀርፋፋ እና ምዕራባዊያኑ መሪዎች የምዕተ ዓመቱን የከፋ የህብረተሰብ ጤና ቀውስ ለመቋቋም ቁርጠኛ አይደሉም ሲሉ ተሟጋቾች ዕቅዱን ተችተዋል።

አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች በዓለም ዙሪያ ወረርሽኙን ለማስቆም በቂ ሰዎች እስኪከተቡ ወራትን ሊጠይቅ ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡

የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ሰኞ ዕለት ስለ ዓለም አቀፍ ክትባት ፍላጎት ተጠይቀው "ከዓለም ጋር የምንጋራው ብዙ ክትባት አለን። ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ ያገኘነው አቅርቦቱ ሳይሆን የሎጂስቲክስ ፈተናው ነው" ብለዋል።