አሜሪካዊው የዓለም ክብረ ወሰንን ለመስበር ባደረገው ሙከራ ወቅት ህይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, facebook
አደገኛ ተግባራት በመሞከር የሚታወቀው የ28 ዓመቱ አሜሪካዊ ዋሽንግተን ውስጥ በሞተር ብስክሌት ረዥም ርቀት በመዝለል የዓለም ክብረ ወሰን ለመስበር ሲሞክር በደረሰበት አደጋ አደጋ ህይወቱ አለፈ።
ባለሥልጣናት እንዳሉት አሌክስ ሃርቪል ሐሙስ ጠዋት ሲለማመድ በደረሰበት አደጋ ነው ህይወቱ ያለፈው።
ሃርቪል በሞሰስ ሌክ ኤይርሾው ውድድር ላይ በተመልካቾች ፊት 107 ሜትር ለመዝለል አቅዶ ነበር ልምምድ ሲያደርግ የነበረው ተብሏል።
የሃርቪልን ህይወት ለሞት ያበቃውን ክስተት በሚያሳየው ቪዲዮ ላይ የሞተር ብስክሌቱ ከታሰበው ዒላማው ፈቀቅ ብሎ የቆሻሻ ክምር ላይ ሲወድቅ ያሳያል።
'ኮሎምቢያ ቤዚን ሄራልድ' የተሰኘው የአካባቢው ጋዜጣ ሃርቪል ከሞተር ሳይክሉ እጀታዎቹ ላይ ሲወድቅ የጭንቅላት መከላከያ ቆቡ ወድቆበት ነበር ብሏል።
የሞሰስ ሌክ ኤይርሾው አዘጋጆች ሃርቪል በደረሰበት ጉዳት ወደ ሆስፒታል መወሰዱን ቢናገሩም በኋላ ላይ የአካባቢው ፖሊስ ቃል አቀባይ ህይወቱ ማለፉን አረጋግጧል።
የግራንት ካውንቲ የፖሊስ ጽህፈት ቤት "ጥልቅ ሐዘናችን ለአሌክስ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና ዘመዶቻቸው ይድረስ" ብሏል።
ባለቤቱ ጄሲካ ከልጆቻቸው ጋር አደጋው በደረሰበት ቦታ የነበረች ሲሆን ላለፉት ሁለት ሳምንታትን በዝግጅት እንዳሳለፈ ገልጻለች። ከሐሙስ የመጀመሪያ ሙከራው በፊት ከፍታውን ለመዝለል አልሞከረም ሲል ኮሎምቢያ ቤዚን ሄራልድ ዘግቧል።
ሃርቪል የሞተር ስፖርት ተወዳዳሪ ሲሆን ቀደም ሲል ሁለት በሞተር ብስክሌት የመዝለል ክብረ ወሰኖችን ይዞ ነበር።
ሃርቪል በኢንስተግራም ገጹ ላይ እየተገነባ ያለው የመዝለያ መንገድ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን ጨምሮ ለቅርብ ጊዜ ያደረገውን ክብረወሰን የመስበር ሙከራ አጋርቷል።
ሃርቪል ባለፈው ወር ከሞሰስ ሌክ ኤይርሾው አዘጋጆች ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ህይወቱን በሙሉ ሞተር ብስክሌቶችን እንደሚወድ እና ዝግጅቱ በሚካሄድበት የአሸዋ ክምር ላይ የመዝለል ልምምድ ማድረጉን ተናግሯል።
የ28 ዓመቱ ሃርቪል ባለትዳር ሲሆን ባለቤቱም ሁለተኛ ወንድ ልጃቸውን በቅርቡ ወለዳለች።
ቤተሰቡን ለመደገፍ በተዘጋጀ የጎፈንድሚ (በበይነ መረብ የሚደረግ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴ ነው) መዋጮ ላይ እስካሁን ወደ 40 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል።












