ዩሮ 2020፡ እግር ኳስ ተጫዋቾች በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የማስታወቂያ መጠጦችን ካነሱ ሊቀጡ ይችላሉ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
በቅርቡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ፖል ፖግባ እንዳደረጉት ተጫዋቾች በጋዜጣዊ መግለጫዎች ወቅት የስፖንሰሮችን መጠጦች ከጠረጴዛ አንስተው ከካሜራ ካራቁ በዩሮ 2020 የሚሳተፉ ቡድኖቻቸው የገንዘብ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል ተባለ።
ሰኞ ዕለት የፖርቹጋሉ አምበል ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት የኮካ ኮላ ጠርሙሶችን ከፊቱ በማንሳት ሰዎች ውሃ እንዲጠጡ አበረታቷል።
በቀጣዩ ቀን ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታይ ሆነው ፈረንሳዊው አማካይ ፖግባ የሄኒከን ቢራ ጠርሙስን ከጠረጴዛው ላይ አንስቷል።
ጣሊያናዊው ማኑዌል ሎካቴሊ ደግሞ ረቡዕ ዕለት ኮካ ኮላ አንስቶ በውሃ ተክቶታል።
ሐሙስ ዕለት "የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (ዩኤፋ) ተሳትፊ ቡድኖች ስፖንሰር አድራጊዎች ለውድድሩ መካሄድ ሚና እንዳላቸው አስታውሶ በመላው አውሮፓ ወጣቶችን እና ሴቶችን ጨምሮ የእግር ኳስ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው" ብለዋል የውድድሩ አዘጋጆች።
የዩኤፋ የዩሮ 2020 የውድድር ዳይሬክተር ማርቲን ካለን በበኩላቸው ተጫዋቾች "የውድድር ደንቦችን ለመጠበቅ በፌዴሬሽናቸው በኩል" የውል ግዴታቸው አለባቸው ብለዋል።
ሆኖም እንደ ፖግባ ያሉ ተጫዋቾች በሐይማኖታዊ ምክንያቶች ያደረጉት በመሆኑ እንደሚረዱት ተናግረዋል።
ቡድኖች የውል ደንቦቻቸውን እንዲያስታውሱ የተደረገ ሲሆን ካለን እንዳሉት ደግሞ የዲሲፕሊን እርምጃም ሌላው "አማራጭ" ነው።
ዩኤፋ በቀጥታ ተጫዋቾችን የመቅጣት ፍላጎት የሌለው ሲሆን ማንኛውም ቅጣት የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ውሳኔ ነው።
"ዩኤፋ ተጫዋቾችን በቀጥታ እየቀጣ አይደለም። ይህን ሁሌም በተሳታፊ ብሔራዊ ማኅበር በኩል ይከናወናል። ከዚያ በኋላ እነሱ ወደ ተጫዋቾቹ የሚሄዱ ከሆነ ማየት ይችላሉ። ለጊዜው በቀጥታ ወደ ተጫዋቾቹ አንሄድም" ብለዋል ካለን።
"በተሳታፊ ፌደሬሽኖች የተፈረሙ ደንቦች አሉን" ብለዋል።












