ምርጫ 2013፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን እንዳይታዘብ ተከለከለ

የኢሰመኮ ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ

የፎቶው ባለመብት, DANIEL/NEBE

የምስሉ መግለጫ, የኢሰመኮ ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) በመጪው ሰኞ በሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለመታዘብ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ቦርዱ ጥያቄውን እንደማይቀበል ገለፀ።

ሰኔ 14/2013 ዓ.ም የሚካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን መታዘብ ከሥራዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን በመግለጽ ጥያቄ ያቀረበው ኢሰመኮ ተቀባይነት ያላገኘው በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው አካላት መካከል ባለመካተቱ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።

ቢቢሲ ከታማኝ ምንጮቹ ያገኘው ደብዳቤ የተሻሻለውን የምርጫ ሕግ በመጥቀስ "ኢሰመኮ የታዛቢነት፣ የጋዜጠኝነት ወይም ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ እና የግል ዕጩ ወኪል ስላልሆነ ቦርዱ የይለፍ ካርድ የሚሰጥበት የሕግ አግባብ ባለማግኘቱ ጥያቄውን ተቀብሎ ማስተናገድ አልቻለም" ሲል ይገልጻል።

ሰኔ 07/2013 ዓ.ም ተጽፎ የቦርዱ አባል በሆኑት በአቶ ውብሸት አየለ ጌጤ የተፈረመው ይህ ደብዳቤ የምርጫ አዋጁን አንቀፅ 123 በመጥቀስ ለተፈቀደላቸው ሰዎች የይለፍ ካርድ እንደሚሰጥ ያብራራል።

አክሎም አንቀፅ 48ን በመጥቀስ ከምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከግል ዕጩ ወኪሎች፣ ከቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት እና ከተፈቀደላቸው ታዛቢዎች ውጪ በምርጫ ጣቢያ ግቢ ውስጥ መገኘት እንደማይቻል ያትታል።

ኢሰመኮ ለቦርዱ ሰብሳቢ ሰኔ 08/2013 ዓ.ም የላከው ደብዳቤ ውሳኔው አግባብ አይደለም፤ በማለት ለቦርዱ ሰብሳቢ አቤቱታውን አቅርቧል።

ይህም የተሻሻለውን የኮሚሽኑን አዋጅ በመጥቀስ ለኮሚሽኑ ከተሰጡት ተግባር እና ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ ምርጫን መታዘብ የሚል እንደሚገኝበት በመጥቀስ ያስረዳል።

ቦርዶ ለኮሚሽኑ በላከው ደብዳቤ ላይ የተሻሻለው የኮሚሽኑ አዋጅ በምርጫ ወቅት ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶችን አጠባበቅ በተመለከተ ክትትል እንዲያደርግ ስልጣን እንደሚሰጠው እንደሚረዳ ገለፆ፤ ነገር ግን ይህንን የመታዘብ ሥራ ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲገባ የሚያስችለው የይለፍ ካርድ ከሚሰጣቸው አካላት ውስጥ የምርጫ አዋጁ አያካትተውም ብሏል።

ይህ በዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የተፈረመው ባለ ሁለት ገፅ ደብዳቤ ከተጠቀሱት 10 ነጥቦች ውስጥ ሁለተኛው "ኮሚሽኑ ይህንን ተግባር እና ኃላፊነቱን የሚወጣው በምርጫ ጣቢያዎች ጭምር በመገኘት ነው" ሲል የሞገተ ሲሆን "ለአብነትም የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆናቸውን ለመረጋገጥ በምርጫ ጣቢያ በመገኘት የሚጣራ ነው" ሲል ጠቅሷል።

አክሎም ዓለም አቀፍ የምርጫ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ እጅግ የተለመደ ነው ያለው ደብዳቤው ይህም ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማትን ያሳተፈ ነው ይላል።

"ቦርዱም የኮሚሽኑን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ማገዝ፣ መርዳት እና ማቀላጠፍ መተባበር የሚጠበቅበት ተግባር ነው" ሲል ዋና ኮሚሽነሩ የጻፉት ደብዳቤ ያስረዳል።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም ሕዝበ ውሳኔ በሚካሄድበት ወቅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባልደረቦች ባጅ ተሰጥቷቸው ሂደቱን መታዘባቸውንም አስታውሷል።

እንዲሁም "የምርጫ ሂደት የበርካታ የሰብአዊ መብቶች መገለጫ ነው ያለው ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች የተከበሩበት ሂደት በሆኑን ተከታትዬ ማረጋገጥ ይገባኛል" ሲል ጠይቋል።

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ማንኛውም ሰው ለኮሚሽኑ ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠት ግዴታ መቀጡን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ቦርዱ ጥያቄውን እንደቀበል ጠይቋል።

የኢሰመኮ የህዝበ ግንኙነት ኃላፊ አሮን ማሾ እንደተረዳው በቦርዱ እና በኮሚሽኑ መካከል ንግግሮች እየተደረጉ መሆኑን አረጋግጠው በደብዳቤዎቹ ላይ ግን አስተያየት ለመስጠት ተቆጥበዋል።

ነገር ግን ይህንን ምርጫ ከሰብአዊ መብቶች አንፃር የተሻለ እንዲሆን በርካታ ተግባራትን ለወራት ማከናወናቸውን እና በምርጫ ቀን ለማከናወን የታቀዱ ተግባራም ከዚህ ጋር የተያያዙ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ይህንን በሚመለከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምልሽን በስልክ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት ያደረገ ቢሆንም ለጊዜው አልተሳካም።

ከአራት ቀናት በኋላ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫን ለመታዘብ የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች እንደሚሰማሩ ተገልጿል።