'የሚስቴን መድኃኒት ተሳስቼ ውጬ ነው' ያለው የአያክሱ በረኛ ቅጣቱ ቀለለት

የአያክስ እና የካሜሩን ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአያክስ እና የካሜሩን ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና

የአያክስ እና የካሜሩን ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና አበረታች መድኃኒት ውስዷል በሚል የተጣለበት ቅጣት እንዲቀልለት ተደርጓል።

ኮርት ኦፍ አርቢትሬሽን ፎር ስፖርት ፍርድ ቤት የኦናና ቅጣት ወደ ዘጠኝ ወራት ዝቅ እንዲል አድርጓል።

የ25 ዓመቱ ግብ ጠባቂ በአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር የ12 ወራት ቅጣት ተጥሎበት ነበር።

ኦናና የታገደ አበረታች መድኃኒት ሰውነቱ ውስጥ የተገኘበት ባለፈው ጥቅምት ድንገተኛ ምርመራ በተደረገለት ወቅት ነው።

ነገር ግን ከተጣለበት ቅጣት በኋላ በስህተት 'አስፕሪን' መስሎት የሚስቱን መድኃኒት እንደዋጠ ተናግሯል።

በዚህም መሠረት የይግባኝ ችሎቱ ቅጣቱን ሙሉ በሙሉ እንዲያነሳለት ቢጠይቅም ችሎቱ ግን ቅጣቱን ማቅለልን መርጧል።

"የካስ ችሎት አንድሩ ኦናና ጥፈተኛ ነው ብሎ አያምንም። ለሌላ ሰው የተዘጋጀን መድኃኒት ነው በስህተት የዋጠው" ይላል የፍርድ ቤቱ መግለጫ።

"በዚህም መሠረት ችሎቱ ግብ ጠባቂው ላሳየው ቸልተኝነት የዘጠኝ ወራት እገዳ በቂ ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህ የሶስት ወራት ማቅለያ አድርጓል። ነገር ግን ግብ ጠባቂው ያቀረበውን ክሱ ይነሳልኝ የሚል ጥያቄ አይቀበልም።"

በካስ ውሳኔ መሠረት የአንድሬ ኦናና ቅጣት በመጪው ኅዳር ይጠናቀቃል።

ኦናና የደች ቻምፒዮን አያክስ አምስተዳርም የቀጣዩ ውድድር ዘመን መክፈቻ ጨዋታን ማድረግ ባይችልም በሚቀጥለው ጥር በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለአስተናጋጇ ሃገሩ ካሜሩን መሰለፍ ይችላል።

ነገር ግን ሃገሩ ካሜሩን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምታደርጋቸውን አራት ጨዋታዎች በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ነው መከታተል የሚችለው።

ካሜሩን ከማላዊ፣ አይቮሪ ኮስት እና ሞዛምቢክ ጋር ተደልድላለች።

ምንም እንኳ በሃገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ መሳተፍ ባይችልም እገዳው ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት ሲቀሩት ወደ ልምምድ ሜዳ መመለስ ይችላል።

የአንድሬ ኦናና ክስ ባለፈው ሳምንት ሲሰማ የአያክሱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኤድዊን ቫን ደር ሳር ይግባኝ እንጠይቃለን ብሎ ነበር።

"አሁን በተሰጠው ፍርድ መሠረት አሁን ተጨማሪ ሶስት ወራቶች አሉን" ብሏል ቫን ደር ሳር ከይግባኙ በኋላ።