ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ የቫይረሱ መነሻ እንደገና ይጠና ማለቷን ቻይና አወገዘች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ የኮቪድ-19 ቫይረስ ከቻይና መነሳት አለመነሳቱን ለመመርመር የምታደርገውን ተጨማሪ ጥረት ቻይና አወገዘች።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በቫይረሱ መነሻ ላይ የደኅንነት ተቋም ሪፖርት ውጤትን ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ አሜሪካንን 'በፖለቲካ ሴራ እና በሌላ ማሳበብ' ከሷል።
ሚኒስቴሩ የኮቪድ-19 እና በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ያለው የቫይረስ ምርምር ቤተ ሙከራ ምንም ግንኙነት የላቸውም ብሏል።
ኮቪድ-19 ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው እአአ በ2019 መጨረሻ በዉሃን ከተማ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ168 ሚሊየን በላይ ሰዎች ባቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 3.5 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
የቻይና ባለሥልጣናት መጀመሪያ አካባቢ የኮቪድ-19 በሽታን በዉሃን ከሚገኘው የባሕር ምግቦች መሸጫ ገበያ ቦታ ጋር አያይዘውት ነበር።
ይህም ተመራማሪዎች ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ጽንሰ ሃሳብ እንዲይዙ መርቷቸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ ከቤተ ሙከራው አፈትልኮ ነው የወጣው ከሚለው ጋር ምንም እንደማይገናኝ አስታውቋል።
ድርጅቱ ይህንን ያለው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የወረርሽኙን መነሻ ለመመርመር ወደ ዉሃን ከተማ ያደረገውን ጉብኝተ ተከትሎ ነው።
የጉዞው አካል የነበሩት የዓለም ጤና ድርጅት የቫይረስ ተመራማሪ ማሪዎን ኩፕማንስ የአሜሪካ ባለሥልጣናት መረጃ ካላቸው ሊያጋሩ ይገባል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ በቅርቡ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ ምን አልባትም በድንገተኛ ክስተት ሊወጣ እንደሚችል አመላክተዋል።
አሁን ውዝግቡ ለምን ተፈጠረ?
ረቡዕ ዕለት ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ "ተህዋሱ ሰዎች በቫይረሱ ከተያዘ እንስሳት ጋር ባላቸው ንክኪ መጣ? ወይስ ከቤተ ሙከራ አፈትልኮ የወጣ ቫይረስ ነው?" የሚለውን ጨምሮ ስለቫይረሱ ሪፖርት እንዲቀርብላቸው ጠይቀው ነበር።
ፕሬዚደንቱ እንዳሉት የደኅንነት አባላቱ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያፈተለከ ነው በሚለው እና ከእንስሳት ወደ ሰው የተላለፈ ነው በሚሉት ሁለት መላ ምቶች ተከፋፍለዋል።
የትኛው ሊሆን እንደሚችል ግን በግልጽ የሚያሳይ በቂ መረጃ እንዳላገኙ ፕሬዝደንቱ አምነዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ተቋማት አቅማቸውን በእጥፍ ጨምረው መረጃዎችን እንዲሰበስቡና እንዲተነትኑ ጆ ባይደን ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ሐሙስ ዕለት ፕሬዚደንት ባይደን የማያውቁት ነገር ከሌለ በስተቀር ያላቸውን ሪፖርት ይፋ እንደሚያደርጉ ማቀዳቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የቫይረሱ መነሻ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመያዝ አሜሪካና ሌሎች አገራት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፉ ድምጻቸውን አስምተዋል።
ይሁን እንጅ ረቡዕ ዕለት የተሰጠው መግለጫ የቻይና ባለሥልጣናትን አስቆጥቷል።
ቻይና፤ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ነው የወጣው የሚለውን መላ ምት አትቀበልም።
የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን "ይህ የሚያሳየው አሜሪካ ስለ እውነት ግድ እንደሌላትና ስለቫይረሱ መነሻ ለሚደረግ ሳይንሳዊ ጥናት ፍላጎት እንደሌላት ነው" ብለዋል።
"ዓላማቸው ወረርሽኙን ማግለልን ለመፍጠር፣ ለፖለቲካ ሴራ እና አንዱ በአንዱ ላይ ጣት እንዲቀስር መጠቀም ነው። ለሳይንስ ፣ ለሰዎች ሕይወት እና ወረርሽኙን ለመዋጋት ለተቀናጀ ጥረት ውጤታማነት ክብር አልሰጡም" ብለዋል።
የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት የተሳሳተን መረጃ በማሰራጨት "ጥቁር ታሪክ " ነው ያላቸው ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ ባወጣው መግለጫም የባይደንን ትዕዛዝ በቀጥታ ባይጠቅስም "የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እና ማሳበብ በድጋሚ ተጀምሯል" ብሏል።












