በጓቲማላ እስር ቤት ውስጥ በተነሳ ፍልሚያ ታራሚዎች ተቀልተው መሞታቸው ተነገረ

የፖሊስ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በጓቲማላ ኩዌትላቴናንጎ በተሰኘ ማረሚያ ቤት ውስጥ በተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል በተነሳ ፍልሚያ ቢያንስ ሰባት እስረኞች መገደላቸውን የጓቲማላ ፖሊስ ገለጸ።

በማረሚያ ቤቱ ውስጥ በተፈጠሩት ማራ ሳልቫትሩቻ እና የባሪዮ-18 በተሰኙ ቡድኖች የአባላት መካከል በተካሄደ ግጭት ነው ሰባቱ ሰዎች አንገታቸው የተቀላው።

ከዋና ከተማው 200 ኪ.ሜ ርቆ የሚገኘው ማረሚያ ቤቱ 500 እስረኞችን ለማኖር የተገነባ ቢሆንም ከ 2000 በላይ ሰዎችን ይዞ ይገኛል።

ወደ 500 የሚጠጉ የፖሊስ መኮንኖች በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የተነሳውን ቀውስ ለመቆጣጠር እንዲሰማሩ መደረጉን የጓቲማላ ብሔራዊ ፖሊስ ቃል አቀባይ ጆርጅ አጉዬላ ተናግረዋል ።

የግጭቱን መነሾ አስመልክቶ አንድ የፖሊስ ምንጭ ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ አቀብለዋል።

አንድ እስረኛ የተቀናቃኙ ቡድን አባል ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ያዘዘ ሲሆን ይህም ባለቤቱ ላይ ተፈፀመ ላለው ግድያ የበቀል እርምጃ ነው ብለዋል ምንጩ።

በባለሁለት እግር ተሸከርካሪ የመጡ ሁለት ሰዎች ግለሰቧን ከሰአታት በፊት ተኩሰው መግደላቸውም ታውቋል።

እንደ ምንጩ ከሆነም ከብጥብጡ በስተጀርባ ያለው ታራሚ በግድያ ወንጀል ተፈርዶበት በእስር ላይ ያለ ነው።

በጓቲማላ በዓመት ከሚመዘገቡት 3 ሺህ ገደማ ከሚሆኑት የግድያ ወንጀሎች መካከል ግማሽ ያህሉ በወሮበላ ቡደኖች ሚፈፀሙ መሆናቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ገልፀዋል።