ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል-ጋዛ፡ ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርጉ ይችላሉ ተባለ
አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የጋዛ ታጣቂዎችና የእስራኤል ባለሥልጣናት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊፈርሙ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡ።
ከዚህ አስተያየት በተቃራኒ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ ትናንት ረቡዕ "ለእስራኤል ዜጎች ሰላምና ደኅንነት እስኪመለስ ድረስ ጥቃቱን እንቀጥልበታለን" ብለዋል።
ሐሙስ ከቀትር በፊት ብቻ ከመቶ በላይ የእስራኤል የአየር ጥቃቶች በሐማስ ወታደራዊ መዋቅር ላይ እንደተተኮሱ ተዘግቧል። በምላሹ የፍልስጤም ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ሮኬት ተኩሰዋል።
የጋዛው ግጭት የተጀመረው በእስራኤልና ፍልስጤማዊያኑ መሀል እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው የምሥራቅ ኢየሩሳሌም አካባቢ በረመዳን ወር ለቀናት ውጥረት ከነገሠ በኋላ ነው።
ሙስሊሞችና አይሁዳዊያን ቅዱስ ቦታችን ነው በሚሉት አል አቅሳ የደማስቆ በር መግቢያ ላይ የእስራኤል ወታደሮች ክልከላ በማድረጋቸው ጋዛን የሚቆጣጠረው ሐማስ ቁጣውን ሲገልጽ ቆይቷል።
ፍልስጤማዊያንም በእስራኤል ወታደሮች የሚደርስባቸው እንግልት እያየለ መምጣቱ ግጭቱን ወደከፋ ደረጃ እያደረሰው መምጣቱ ይታወሳል።
ነገሮች እየተጋጋሉ መጥተው ሐማስ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፍ መጀመሩን ነው ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆነው ግጭት የተጀመረው።
እስከአሁን በነበረው መጠነኛ ጦርነት በትንሹ 227 ፍልስጤማዊያን በጋዛ ተገድለዋል። ከነዚህ ውስጥ 100 የሚሆኑት ሕጻናትና ሴቶች ናቸው።
እስራኤል በበኩሏ 150 የሚሆኑት የጋዛ ሟቾች የሐማስ ታጣቂዎች ናቸው ትላለች።
ሐማስ የሞቱበትን ተዋጊዎቹን ቁጥር ለጊዜው ይፋ አላደረገም። ሆኖም ቁልፍ ወታደራዊ መኮንኖቹ እንደሞቱበት ይገመታል።
በእስራኤል በኩል የሟቾቹ ቁጥር 12 ብቻ ሲሆን ከነዚህ መሀል ሁለቱ ሕጻናት ናቸው። ሆኖም ወደ እስራኤል የተወነጨፉት የሮኬቶች ብዛት ከ4ሺህ ይልቃሉ። ከነዚህ ውስጥ 99 ከመቶ የሚሆኑት በእስራኤል ጸረ ሮኬት ሲስተም የመከኑ እንደሆኑ እስራኤል ትናገራለች።
በቅርብ ሰዓታት ውስጥ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሙሳ አቡ መርዙቅ ለሊባኖሱ ማያዲን ቲቪ በሰጡት ቃለምልልስ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ፈር እየያዘ እንደመጣ ጠቁመዋል። "ከሁለት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ስምምነት የምናደርግ ይመስለኛል"› ብለዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ በጋራ መግባባት ላይ የሚመሠረት እንደሆነም አብራርተዋል። ይህ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን አስተያየት የተሰማው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱ ተዋጊዎች የንጹሐንን እልቂት እንዲያቆሙ ጫና እየደረሰባቸው ባለበት ወቅት ነው።
አንድ የግብጽ የደኅንነት ምንጭ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ድርድሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ትናንት ረቡዕ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለ4ኛ ጊዜ ወደ ናታንያሁ ስልክ መተው በጉዳዩ ላይ ተወያይተዋል። ሁለቱን ወገኖች የማደራደር ሂደቱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ዛሬ ጠዋት እስራኤል የአየር ጥቃት ማድረጓ ተዘግቧል።
በዚህ ጥቃት ሁለት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ አውድማለች። በዚህ ጥቃት በካን ዩኒስ ከተማ አራት ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል የሕክምና ምንጮች።
እስራኤል በበኩሏ ይህ የዛሬው ጥቃት ሐማስ ሮኬት የሚያከማችባቸውና የሚተኩስባቸው ግቢዎችን ያለመ ነበር ብላለች።
በእስራኤል ከተማ ቢርሼባ አሁንም የማስጠንቀቂያ ደውሎች ተከታትለው እንደሚሰሙ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመላክታል።