በምዕራብ ኦሮሚያ 'ሦስት ቻይናውያን ታግተዋል የተባለው ሐሰት ነው'

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ሦስት ቻይናውያን የማዕድን አውጪ ኩባንያ ሠራተኞች በታጣቂዎች ታግተዋል መባሉን ሐሰት ነው ሲሉ የዞኑ ባለሥልጣን አስተባበሉ።
እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራ ቡድን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ አቅራቢያ ሦስት የቻይና ዜጋ የሆኑ የማዕድን ሠራተኞችን አግቼ ይዣለሁ ብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ የምዕራብ ወላጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዞኑ ውስጥ ታግቶ የሚገኝ የውጭ ዜጋ የለም በማለት ቡድኑ ያወጣው መግለጫ ሐሰት ነው ብለዋል።
አቶ ኤልያስ ጨምረውም "በዞኑ ውስጥ ታግቶ የሚገኝ ቻይናዊ አለመኖሩን አረጋግጫለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ ጥቃቶችን እንደሚፈጽም የሚነገረውና መንግሥት 'ሸኔ' እያለ የሚጠራው ቡድን በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ቡድን ተብሎ መፈረጁ ይታወሳል።
ይህ ቡድን ባለፈው ቅዳሜ በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ አቅራቢያ በማዕድን ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሦስት የቻይና ዜጎችን አግቼ ይዣላሁ ማለቱ ይታወሳል።
በመግለጫው ተፈጸመ ላለው እገታ ምክንያቱ "በመንግሥት እና በማዕድን አውጪዎቹ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ሕጋዊ አይደለም" የሚል ነው።
ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተገንጥሎ የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የሚገልጸው ይህ ቡድን በአካባቢው የሚደረገው የማዕድን ቁፋሮ በርካቶችን ከቀያቸው አፈናቅሏል፣ በአካባቢያዊ ላይም ጉዳት እያስከተለ ነው ብሏል።
ይህ ቡድን ሦስት ቻይናውያን ማዕድን አውጪ ሠራተኞችን አግቼ ያዝኩ ይበል እንጂ ሦስቱ ቻይናውያን የሚሰሩበት ድርጅት ማንነት፣ በየትኛው የማዕድን ማውጣት ተግባራት ላይ ተሰማርተው እንደነበረና የቻይናውያኑ ኃላፊነት ምን እንደሆነ ያለው ነገር የለም።
የታጣቂ ቡድኑ ነው ከተባለው መግለጫ ጋር ታግተዋል የተባሉ የሦስት ሰዎች ፎቶግራፍ የተሰራጨ ቢሆንም ስለግለሰቦቹ ማንነት የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ ግን አልተገኘም።
ጉዳዩን በተመለከተ ባለፉት ጥቂት ቀናት ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ አዲስ አበባ ከሚገኘው የቻይና ኤምባሲ የተባለ ነገር የለም።
የአካባቢው ባለስልጣናት ምን ይላሉ?
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የምዕራብ ወላጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ፤ እገታውን በተመለከተ "በማኅበራዊ ሚዲያ የተባለውን አንብበናል፤ ውሸት ነው። አረጋግጠናል" ብለዋል።
"በወረዳችን፣ በቀበሌያችን መሰል ነገር አለመከሰቱን አረጋግጠናል" ያሉት አቶ ኤልያስ፤ ጨምረውም በአካባቢው የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ ቻይናውያን አለመታገታቸውን እንዳረጋገጡ ተናግረዋል።
መንዲ ከተማ የቱርክ እና የሕንድ ዜጎች ማዕድን የማውጣት ሥራ ተሰማርተው እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ኤልያስ፤ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዘወትር በሥራ ገበታቸው እንደማይገኙ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የመነ ሲቡ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ ታመነ ይህ ክስተት እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ወረዳ አለመከሰቱን ተናግረው፤ "በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኦዳ ቢልዲጊሉ ወረዳ እገታው ተፈጽሟል" የሚል መረጃ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህን በተመለከተ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው ነገር የለም።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው ስለ ጉዳዩ የማውቀው የለም ብለዋል።
"ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የውጭ አገር ዜጎች ታፍነዋል የሚል መረጃ የለኝም። ኦሮሚያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ መረጃው ይደርሰን ነበር" ብለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት መንዲ ከተማ አቅራቢያ ታጣቂዎች ፈጸሙት በተባለ ጥቃት ሁለት የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ አምስት ማዕድን አውጪዎች መገደላቸው ይታወሳል።

በምዕራብ እና ደቡብ የኦሮሚያ አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል።
ለእነዚህ ጥቃቶችም ለረጅም ዓመታት በትጥቅ ትግል ላይ ከነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የወጣውና እራሱን 'የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት' ብሎ የሚጠራው እና በመንግሥት ደግሞ 'ሸኔ' የተባለው ቡድን ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡድኑን የሽብር ቡድን አድርጎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መሰየሙ ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል በዚህ ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 18 የመንግሥት ባለስልጣናት፣ 112 የፖሊስ አባላት እና 42 የሚሊሻ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።















