የሚንስትሮች ምክር ቤት 'ሕወሓት እና ሸኔ' በሽብርተኛነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ አስተላለፈ

የሚንስትሮች ምክር ቤት አባላት

የፎቶው ባለመብት, Office of the PM

የሚንስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ሸኔ በሽብርተኛነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ማስተላለፉን የጠቅላይ ሚንስትሩ ጸ/ቤት አስታወቀ።

ሁለቱ ቡድኖች ባለፉት ሦስት ዓመታት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል ብሏል ጸ/ቤቱ።

"በዚህም የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ ከቀዬአቸውም ተፈናቅለዋል። ጥቃቶቹ ህብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው ሥጋት እና ፍርሐት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ አድርጓ።"

"እነዚህ ሁሉ የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ታቅደው ሲፈጸሙ የነበሩ መሆኑን ከተለያዩ ማስረጃዎች ለመረዳት ተችሏል" ብሏል በመግለጫው።

የጠቅላይ ሚንስቴሩ ጸ/ቤት በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ የቆዩት ጥቃቶች በተለያዩ አካላት ቢፈጸሙም "በዕቅድ፤ በገንዘብ፣ በሐሳብ እና በሰው ኃይል ሥልጠና በመደገፍ፤ የሚዲያ ሽፋን እና እገዛ በመስጠት ረገድ የመሪነት ሚናውን ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖች አሉ" ብሏል።

"ኢትዮጵያን የማመሰቃቀል፤ የማዳከም እና የማፍረስ ፍላጎት ያላቸው" ናቸው ያላቸው 'የውጭ ኃይሎች' ቡድኖቹን እየተጠቀሙባቸው ነው ሲልም አስታውቋል።

"ድርጅቶቹ ሲፈጸሙና ሲያስፈጽሙ የቆዩዋቸው የጥፋት ተግባራት የሽብር ወንጀል ተግባራት ናቸው። እነዚህ ተግባራት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አወጅ 1176/2012 አንቀጽ 3 ሥር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ ለሙሉ የሚያሟሉ ተግባራት እንደሆኑ በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል" ብሏል።

የሽብር ተግባራቱን የፈጽሙ ድርጅቶች አባላትና እና ደጋፊዎቻቸውን በግለሰብ ደረጃ በተናጠል በሽብር ወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ "ድርጅቶቹን የሽብርተኛ ድርጅት አድርጎ በመሰየም በሕጉ በተቀመጠው አግባብ የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይችላል" ብሏል በመግለጫ።

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 18 እና 19 በመጥቀስ "ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)" እና "ሸኔ" የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑና የድርጅቶቹ የሥራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጭ አካላት ወንጀሉን አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት በመሆኑ፤ የሽብር ተግባር መፈጸምም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል" ብሏል።

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 23 መሠረትም "በተመሳሳይ ተግባር በተሰማሩ እና በዚህ ውሳኔ ሐሳብ መሠረት ከተሰየሙት የሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ትብብር፤ ትሥሥር ወይም የሐሳብ እና የተግባር ዝምድና ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይም ይህ ውሳኔ ሐሳብ ተፈጻሚ ይሆናል" ሲል አጠናቋል።