ቢያንስ 15 ሰዎች በተገደሉበት ጥቃት ታጣቂዎች "ሰዎችን በቋንቋ ችሎታ ለይተዋል"

ቡሬ ከተማ ከፍኖተ ሰላም ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች
የምስሉ መግለጫ, ቡሬ ከተማ ከፍኖተ ሰላም ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች

ትናንት ቢያንስ 15 ሰዎች በተገደሉበት ጥቃት ሰዎች ከአውቶብስ ወርደው በቋንቋ ችሎታቸው መለየታቸውን አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከምዕራብ ጎጃም ቡሬ ከተማ ወደ ነቀምት መስመር ሲጓዝ በነበረ የሕዝብ ማመላለሽ አውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸውን ኢቢሲ ፖሊስ ጠቅሶ ዘግቧል።

የሆሮ ጉዱሩ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ብርሃ የባሳ ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው፤ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተሳፋሪዎችን ከአውቶብስ እንዲወርዱ ካደረጉ በኋላ ቢያንስ 15 ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከሟቾች በተጨማሪ በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፤ ድርጊቱ እየተጣራ ነው ብለዋል።

የፖሊስ አዛዡ ከሟቾቹ መካከል የኦሮሞ እና የአማራ ብሔር ተወላጆ ይገኙበታል ብለዋል።

የዓይን እማኙ ምን ይላሉ?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዓይን እማኝ በአውቶብሱ ተሳፍረው የነበሩት አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች መዳረሻቸው ምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ውስጥ ወደምትገኝ ጉትን ከተማ መሆኑን ያስረዳሉ።

ጉትን ከተማ ከነቀምቴ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች የሚኖሩባት አስተኛ ከተማ ነች።

የዓይን እማኙ ረፋድ ላይ በባለ ሁለት በር የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተሳፍረው ከቡሬ ከተማ መነሳታቸውን ያስታውሳሉ።

የአባይ በረሃን ጨረሰው እንደወጡ ወደ 20 የሚሆኑ እና የተለያዩ አይነት መሳሪያዎችን የታጠቁ ሰዎች አውቶብሱን እንዳስቆሙት ይናገራሉ።

"ግማሹ ቦታ ቦታ ይዘው ቆመዋል። ግማሹ ደግሞ ከመኪናው አስወረዱን። ከዛ የሰዎችን ዘር መለየት ጀመሩ" ይላሉ ይህ የዓይን እማኝ።

ታጣቂዎቹ ተሳፋሪዎችን በኦሮምኛ 'ማን ነህ?' 'ወዴት ነው የምትሄደው?' የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ መጀመራቸውን የዓይን እማኙ ያስረዳሉ።

"ኦሮምኛ የምንችል ኦሮምኛ ተናግረን አለፈን። ኦሮምኛ የማይችሉትን ለይተው ወደ ጫካ ይዘው ሄዱ። ብዙ ሰው ይዘው ሄደዋል"።

የዓይን እማኙ እንደሚያስረዱት ተሳፋሪዎች ከአውቶብሱ እንዲወርዱ ተደርጎ ታጣቂዎቹ ተሳፋሪዎችን እየጠየቁ ሳለ አራት ሰዎች ለማምለጥ ሲሮጡ ታጣቂዎቹ ተኩሰው እንደገደሏቸው ይናገራሉ።

ከአራቱ ሰዎች ውጪ ግን የተለዩት ሰዎች ሲገደሉ አለማየታቸውን አስረድተዋል። "ወደ ጫካ ይዘዋቸው ሲሄዱ ነው ያየሁት። ጉቲን ከተማ ከደረሰን በኋላ ነው የወሰዷቸውን ሰዎች እንደገደሏቸው የሰማነው" ይላሉ።

ታጣቂዎቹ ተሳፋሪዎቹን ከአውቶብሱ ካስወረዱ በኋላ፤ አውቶብሱ ወደ ቡሬ መመለሱን ይህ የዓይን እማኝ ይናገራሉ።

"በአውቶብሱ ከነበርነው ውስጥ 26 ሰዎችን ነው ለይተው የለቀቁን። ሁለት ረዳቶች እና ሹፌሩ ወደ ቡሬ ተመልሰዋል። አራቱን ገድለው የተቀሩትን ወደ ጫካ ይዘው ሄደዋል" ይላሉ የዓይን እማኙ።

ይህ የዓይን እማኝ ታጣቂዎች በትክክል ስንት ሰው ለይተው እንደወሰዱ ባያውቁም ከ30 የማያንሱ ሰዎችን ወደ ጫካ ይዘው ስለመሄዳቸው ይናገራሉ።

አውቶብሱ ወደ ቡሬ ዞሮ ከተመለሰ በኋላ ወደ ነቀምት መስመር በእግር ጉዞ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

"አውቶብሱ ከተመለሰ በኋላ በእግር ጉዞ ጀመርን። መንገድ ላይ አይሱዙ መኪና አግኝተን አጋምሳ እስከሚባል ቦታ አደረሰን" በማለት ያስረዳሉ።

ይህ የዓይን እማኝ ኦሮምኛ መናገር መቻላቸው ከጥቃቱ እንዲያመልጡ ቢያስችላቸውም፤ በርካቶች በብሔራቸው ምክንያት ተለይተው መገደላቸው ከፍተኛ የሆነ ድናጋጤን እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ።

"ከድንጋጤ የተነሳ ትናንት መናገር ሁሉ አልቻልኩም ነበር። ምንም ቃል ማውጣት ተስኖኝ ነበር። ዛሬ ነው መናገር የጀመርኩት ሲሉ" ገጠመኛቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

line

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ማንነት መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ይገኛሉ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና አማራ መሰል ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

በተመሳሳይ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ወደ አማራ ክልል እየጓዙ በነበሩ የአይሱዙ የጭነት መኪኖች ላይ በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውን የአከባቢው ባለስልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።