የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያራዝመውን ውሳኔ ቀለበሱ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋራማጆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋራማጆ የሥልጣን ዘመናቸውን በሁለት ዓመት ለማራዘም እያደረጉት የነበረውን ሙከራ መተዋቸውን ተነገረ።

ፕሬዝዳንቱ ምርጫ ሳይደረግ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ውሳኔ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ጎሳን መሠረት ባደረጉ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል።

ውጊያውፕ ሬዝዳንት ፋርማጆን በሚደግፉና በሚቃወሙ የሠራዊት አካላት አልያም በታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ነው።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለአገሪቱ ሕዝብ በተላለፈ ንግግር አዲስ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አድርገዋል።

ጨምረውም የሥልጣን ጊዜያቸው ካበቃበት ከየካቲት ወር ጀምሮ ሲቃወሟቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ውዝግቡ ከተጀመረ በኋላ ላደረጉት አወንታዊ ጥረት አመስግነዋቸዋል።

ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በመጪው ቅዳሜ በአገሪቱ ፓርላማ ቀርበው ሊካሄድ ታቅዶ በነበረው ምርጫ ዙሪያ ባለፈው መስከረም የተደረሰውን ስምምነት ወደነበረበት እንዲመለስ ያደርጋሉ ተብሏል።

በዚህም ከሳምንታት በፊት የምክር ቤት አባላት የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን ለሁለት ዓመት እንዲራዘም ያስተላለፈው ውሳኔ የሚሻር ይሆናል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በተደረሰው ስምምነት የአገሪቱ ጎሳ መሪዎች ተወካዮቻቸውን ከመረጡ በኋላ እነሱም በበኩላቸው የአገሪቱን ፕሬዝዳንት የሚመርጡ የፌደራሉ የምክር ቤት አባላትን ይሰይማሉ።

"ከዚህ በፊት እንዳደረኩት አሁንም በሶማሊያ ውስጥ በወቅቱና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ምርጫ እንዲደረግ ያለኝን ፍላጎት በድጋሚ ላረጋግጥ እወዳለሁ" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ጨምረውም የአገሪቱ የጸጥታ ተቋማት የሠላማዊ ሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ "የአገሪቱን መረጋጋት ከሚያውክ ድርጊቶች" እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ዘመን መራዘም ተከትሎ በሞቃዲሾ ውስጥ ባሉ ታጣቂዎች መካከል በለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተፈጠረውን ግጭት በመሸሽ ነዋሪዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ ነው።

በተጨማሪም የተከሰተው አለመረጋጋት ታጣቂው እስላማዊ ቡድን አል ሻባብ ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።