የኢራኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በድብቅ በተቀዳ ድምፅ የመንግሥታቸውን ጉድ አወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንድ ሾልኮ የወጣ የድምፅ ቅጂ የኢራኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ አይነኬ የሚመስለውን አብዮታዊ ዘብ ሲተቹ አሰምቷል።
ሚኒስትሩ አብዮታዊው ዘብ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን እንደተቆጣጠረ እንዲሁም ኢራንን ወደ ሶሪያ ጦርነት እንዳስገባት ያወራሉ።
በርካቶች 'አፋቸውን በመዳፋቸው ይዘው' ባደመጡት የድምፅ ቅጂ ሚኒስትሩ በሶሪያ ጦርነት ኢራን የሩስያን ዱካ እየተከተለች እንዳለ ይናገራሉ።
በበርካታ ኢራናዊያን ዘንድ አምባገነናዊ ባሕርይ የላቸውም ከሚባሉት ጉምቱው ዲፕሎማት ዛሪፍ አፍ ይህ መውጣቱ ብዙዎችን አስደንቋል።
ድምፁን ማን ቀድቶ እንደለቀቀው ባይታወቅም ኢራን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ደፋ ቀና በምትልበትና ፖለቲካዊ ጨዋታው በደራበት ወቅት መለቀቁ ጥርጣሬ ጭሯል።
ሚኒስትር ዛሪፍ ፕሬዝደንት ሀሳን ሩሃኒን የመተካት ሐሳብ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ነገር ግን ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩን እንደማያምኗቸው ይነገራል።
ወጣም ወረደ የድምፅ ቅጂውን ተከትሎ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አደጋ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታ ይመስላል።
የአገሪቱ ቁጥር አንድ የፀጥታ ኃይል የሆነው አብዮታዊው ዘብን ጨምሮ ሁሉንም የመንግሥት ጉዳዮች በበላይነት የሚቆጣጠሩት አያቶላ አሊ ካሚኒ ምን ዓይነት ፍርድ እንደሚሰጡ አይታወቅም።
የሦስት ሰዓት ርዝማኔ ያለው የድምፅ ቅጂ ለቢቢሲና ለሌሎች የዜና ተቋማት ተልኳል።
ቅጂው የፕሬዝደንት ሩሃኒን የሥልጣን ዘመን አስመልክቶ ከሁለት ወራት በፊት ከተሠራ አንድ የታሪክ ፕሮጀክት ላይ እንደተወሰደ መረዳት ተችሏል።
ዛሪፍ በተደጋጋሚ ለዓመታት ሐሳብ አስተያየታቸው ሰሚ እንደሌለውና እንደማይታተም ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ሚኒስትሩ አብዮታዊው ዘብ ዲፕሎማሲና የኢራን ውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ቀጠናዊ የኃይል ግፊያን ለመቆጣጠር እየተጠቀመበት እንደሆነ ሲያማርሩ ይሰማሉ።
ሚኒስትሩ እንደሚሉት በአሜሪካ የድሮን ጥቃት የተገደሉት የቀድሞው የአብዮታዊው ዘብ የኩድስ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ቃሲም ሱሊማኒ ናቸው የሩስያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ስለፈለጉ ብቻ ኢራንን ወደ ሶሪያ ጦርነት የከተቷት።
አክለው ሱሊማኒ የኢራን ብሔራዊ አየር መንገድ የሆነው ኢራን ኤርን ይዘው ወደ ሶሪያ ጦርነት አምርተዋል በማለት በሶሪያው ጦርነት የመንገደኞች አውሮፕላን ጥቅም ላይ መዋሉን አረጋግጠዋል።
ዛሪፍ አክለውም፤ የሩስያው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ኢራን በፈረንጆቹ 2015 ሩስያን ጨምሮ ከስድስት ኃያላን አገራት ጋር የኒውክሌር ስምምነት እንዳትደርስ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል ብለዋል።
እንደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሆነ ኢራን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሰላም እንድትፈጥር ሩስያ አትሻም።
ሚኒስትሩ ከሩስያው አቻቸው ላቭሮቭ እንዲሁም አገራቸው ኢራን የሩስያ አጋር እንደሆነች ቢታሰብም የዛሪፍ ሐሳብ ብዙዎችን አስደንቋል።
ኢራን እና ዩናይትድ ስቴትስ የኒውክሌር ስምምነቱን በሚያንሰራሩበት መንገድ ዙሪያ ቪዬና ውስጥ እየመከሩ ይገኛሉ።
አሜሪካ በዶናልድ ትራምፕ ዘመን ኢራን ላይ ማዕቀብ መጣሏን ተከትሎ ኢራን ስምምነቱን ማፍረሷ የሚዘነጋ አይደለም።
ሚኒስትር ዛሪፍ እንደሚሉት አብዮታዊው ዘብ ስምምነቱን በፍፁም አይፈልገውም፤ ተግባራዊ እንዲሆንም አይሻም።
ለዚህ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት አንድ ሚሳዔል በሚሞከርበት ወቅት አብዮታዊው ዘብ "እስራኤል ከምድረ-ገፅ መጥፋት አለባት" የሚል ፅሑፍ በሂብሪው ማስፃፉንና በ2016 በባሕረ ሰላጤው ላይ 10 የአሜሪካ የውቅያኖስ አሳሾችን ማገቱን ነው።
አብዮታዊው ዘብ በበርካታ ጉዳዮች የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩን እንደማያማክሯቸው ሚኒስትሩ አጋልጠዋል።
አሜሪካ ሱሌማኒን ከገደለች በኋላ ኢራን በአፀፋው ኢራቅ ውስጥ አሜሪካዊያን ያሉበት ወታደራዊ ካምፕን ማጥቋቷን አውስተው ስለ ጉዳዩ የሰሙት ከጥቃቱ ሁለት ሰዓት ቀደም ብሎ እንደሆነ ይናገራሉ።
የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የዛሪፍ አስተያየት ከአውድ ውጭ እንደተወሰደ ተናግረው አስፈላጊ ከሆነ ሙሉ ቃለ ምልልስ እንደ አዲስ እንደሚለቀቅ ተናግረዋል።












