ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ፡ በአድዋ 'የኤርትራ ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ' ነዋሪዎች መገደላቸው ተገለጸ
በአድዋ ከተማ ሚያዚያ 04/2013 ዓ.ም፣ ሰኞ ረፋድ አካባቢ የኤርትራ ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ ነዋሪዎች እንደተገደሉና እንደቆሰሉ ተገለጸ።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአክሱምና የማዕከላዊ ዞን ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዳሉት ተኩሱ በኤርትራ ወታደሮች መከፈቱን ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ በዚህም ሳቢያ ቢያንስ አንድ ሰው እንደሞተ ሲናገሩ ነዋሪዎች ግን ቁጥሩ ስምንት ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ደግሞ በክስተቱ ሦስት ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውንና ቢያነስ 19 ሰዎች መቁሰላቸውን ማረጋገጡን ለቢቢሲ ገልጿል።
ድርጅቱ ጨምሮም ይህ ሁኔታ የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ያመለክታል ብሏል።
ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀው የአክሱም ሆስፒታል ዶክተር ከትናንት ረፋድ ጀምሮ እስከ ከሰዓት በኋላ ድረስ 20 የቆሰሉ ሰዎች ከአድዋ እንደመጡ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ማኅበር (ኤምኤስኤፍ) እንዳለው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ከአድዋ ሆስፒታል እንዳመጣቸው የሚናገረው ይህ ዶክተር "ሁለት ሴቶች የሚገኙባቸው 20 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እያከምን ነው" ብሏል።
ኤምኤስኤፍ በበኩሉ ትናንት በትዊተር እንደገለጸው ሰኞ እለት 18 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ አድዋ ኪዳነምህረት ሆስፒታል እንደመጡና እርዳታ እንደተደረገላቸው በመጥቀስ፤ 11 ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለከፍተኛ ህክምና ወደ አክሱም ሆስፒታል ተልከዋል ብሏል።
"ወታደሮቹ ጥቃት በደረሰባቸው ሰዎች ላይ መተኮሳቸው ነግረውኛል" ብሏል።
የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ስድስቱ ከፍተኛ ጉዳት ስለ ደረሰባቸው በጽኑ የህክምና ክትትል ውስጥ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ አንዷ ሴት እንደሆነች ቢቢሲ ያነጋገረው ሐኪም ገልጿል።
የህክምና ባለሙያው እንደሚለው አንዳንዶቹ ሆዳቸው ላይ፤ የተቀሩት ደግሞ በተለያየ የሰውነታቸው ክፍል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
እነዚህ በ20ዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆን አንድ በ60ዎቹ የሚገኙ ግለሰብ እንደሆኑ ለማወቅ ችለናል።
ጥቃቱ በአድዋ መናኽሪያ በመባል በሚታወቀው አካባቢ እንደሆነ ያረጋገጡልን በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአክሱምና የማዕከላዊ ዞን ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስገዶም ስዩም፤ በመኪና ተጭነው ሲሄዱ የነበሩት የኤርትራ ወታደሮች "አንድ የባጃጅ አሽከርካሪ መንገድ ዘጋብን" በሚል ጥቃት እንደፈጸሙ ተናግረዋል።
"ባለ ባጃጁ ጉዳት ደርሶበታል፤ አንድ ሰው እንደሞተም መረጃው ደርሶኛል። ሌሎች አምስት ሰዎች ደግሞ ተመትተው አክሱም ሪፈራል ሆስፒታል ይገኛሉ" ብለዋል።
በተጨማሪም "የአክሱም ሕዝብም ሲሮጥ ነው የዋለው፤ የኤርትራ ወታደሮች ያገኙትን ሰው እየገደሉ እየመጡ ነው የሚል ስልክ ወደ አክሱም ተደወለ። ሕዝቡም ንብረቱን ትቶ፣ የከፈተው ሱቅ ሳይዘጋ ሸሸ" ሲሉ አቶ አስገዶም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ የኤርትራ መንግሥት የሰጠው ማብራሪያ የለም።
በጉዳዩ ላይ የትግራይ ግብረ ኃይል ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ዮሐንስ ገብረመስቀልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ባለፈው ሳምንት ግን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው የገቡት የኤርትራ ወታደሮች መውጣት እንደጀመሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጾ ነበር።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተጠቂዎችና ኗሪዎች እንደሚሉት የኤርትራ ወታደራዊ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ጥቃት እንደፈፀሙ ነው።
የአካል ጉዳት ደርሶበት አክሱም ሆስፒታል ላይ ከሚገኙት ታካሚዎች አንዱ የሆነው በጸጉር ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት፤ ሰኞ ጠዋት ወደ ሥራ እየሄደ ዲጋዲግ ተብሎ በሚጠራው የአውቶብሶች መናኽሪያ መኪና ላይ ሆነው የሚተኩሱ የኤርትራ ወታደር ልብስ የለበሱ ወታደሮች በጥይት እንደመቱት ለቢቢሲ ገልጿል።
"ሁለት የኤርትራ ሠራዊት የጫኑ የጭነት መኪኖች አንበሳ ባንክ አካባቢ ሲደርሱ መተኮስ ጀመሩ። አጋጣሚ አጠገቤ አንድ ሱቅ ነበርና ወደ እዚያ ልገባ ስሮጥ ሦስት ጊዜ ተኮሱብኝ። ሁለት ከጀርባዬ አንድ ደግሞ ሆዴ ላይ መታኝ።"
ተመሳሳይ ቆስሎ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው ሌላ ታካሚ አምስት ጥይት እንደተተኮሰበት በመግለጽ "አንዱ አንገቴ አካባቢ፣ ሦስት ከጀርባዬ፣ አንድ ደግሞ እጄን መቶኛል" ብሏል።
ሰኞ እለት ጥቃቱ ሲፈጸም አካባቢው ላይ ማን ነበር ብሎ ቢቢሲ የጠየቀው ሌላ የአድዋ ከተማ ኗሪ በበኩሉ" ወታደሮቹ ወደ ከተማዋ ሲገቡ፣ ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት አድዋ ላይ ምንም አይነት ጦርነት አልነበረም" ብሏል።
ከሰሞኑ የኤርትራ ሠራዊትን አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ሲነሳ ለነበረው የኤርትራ ሠራዊት ተሳትፎ ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህም የኤርትራ ሠራዊት በድንበር አካባቢ "የደኅንነት ስጋት እንዳለበት" ገልጾ በዚያው አካባቢ ሠራዊቱ እንዳለ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፣ ለዚህም ምክንያቱ "በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ በህወሓት የተፈጸመው ጥቃት እንደሆነ" ተናግረው ነበር።
በዚሁ ወቅት በተጨማሪ ትግራይ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰትና በደሎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰው መንግሥታቸው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
"እኛ ወታደሩን የላክነው ወንጀለኞችን እንዲቆጣጠር እንጂ እንዲደፍር አይደለም። በዚህ ወንጀል የተሰማራ ወታደር ካለ በሕግ ተጠያቂ ይደረጋል" ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው መቃቃርና አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።
በትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አሃዙ በበርካታ ሺዎች ሊሆን እንደሚችል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይናገራሉ።
ከዚህ ባሻገርም በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች ግድያዎች፣ ጾታዊ ጥቃቶች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ዘረፋና የንብረት ውድመቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ አመልከተዋል።
በተጨማሪም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዳለው በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።