የፊደል ካስትሮ ወንድም ራውል ካስትሮ ከኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ መሪነት ለቀቁ

የፊደል ካስተሮ ወንድም ራውል ካስትሮ ከኩባ ብቸና ገዢ ፓርቲ ሊቀመንበርነት ለቀቁ።

ራውል ካስትሮ ከደሴቲቱ አገር ኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ መሪነታቸው መነሳታቸውን ሲገልጹ ቤተሰቦቻቸው ለስድስት አስርት ዓመታት የቆየበትን የሥልጣን ጊዜ አጠናቋል።

የ89 ዓመቱ ካስትሮ አመራሩን "በጋለ ስሜት እና በፀረ-ኢምፔሪያሊዝም መንፈስ ለተሞላ" የወጣቱ ትውልድ እንደሚያስተላልፉ ለፓርቲው ጉባኤ ተናግረዋል።

ተተኪያቸውም ለአራት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ መገባደጃ ላይ ይመረጣል።

እርምጃው በ1959 አብዮት የጀመረው የእርሳቸው እና የወንድማቸው ፊደል ካስትሮ የመሪነት ዘመን ማብቂያ ይሆናል።

ካስትሮ አርብ ዕለት በሃቫና ለተገኙ የፓርቲው ልዑካን "እኔ በአገሬ ሰዎች ጥንካሬ እና አርአያነት ባለው ተፈጥሮ እና ግንዛቤ በጣም አምናለሁ" ብለዋል።

ካስትሮ ተተኪያቸውን ባያሳውቁም የፓርቲው አመራር እአአ በ2018 የደሴቲቱን ፕሬዝዳንትነት ለተረከቡት ሚጉኤል ዲያዝ-ካኔል ኃላፊነቱን ይተላለፋል የሚል ሰፊ እምነት አለ።

የዘመን ፍጻሜ

የእርሳቸው ከኃላፊነት መነሳት ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላ፤ ኩባ ለመጀመሪያ ጊዜ የካስትሮ ቤተሰብ አባል የፖለቲካ መሪዋ አይሆንም ማለት ነው።

ራውል እአአ በ2011 ታላቅ ወንድማቸው ፊደልን በመተካት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል።

ፊደል ካስትሮ እአአ በ1959 የኩባን መንግሥት ከሥልጣን ያወረደውን የኮሚኒስት አብዮት የመሩ ሲሆን ራውል ደግሞ ከአዛዦቻቸው አንዱ ሆነው አገልግለዋል።

ፊደል ካስትሮ በ2006 እስከታመሙበት ጊዜ ድረስ የአገሪቱ መሪ ነበሩ። ይሁን እንጂ በ2008 ፕሬዝዳንትነቱን ለወንድማቸው አስረክበዋል። ከዚያም እአአ በ2016 ፊደል ካስትሮ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ኩባ በራውል ስር

ራውል ካስትሮ እንደ መሪ የኮሚኒስትን የአንድ ፓርቲ የሥልጣን ጉዞ እንዲቀጥል አደረጉ።

በ2014 ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር የተደረገውን ታሪካዊ ውይይትን ጨምሮ ከ 2014 እስከ 2016 መካከል ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነቶች መሻሻልን በበላይነት መርተዋል።

ማዕቀቡን ባጠናከረው በዶናልድ ትራምፕ ዘመን ግን ውጥረቱ ተባብሷል።

የዋይት ሐውስ በኩባ ፖሊሲ ላይ የሚደረግ ለውጥ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አለመሆኑን ቢጠቅስም፤ የወቅቱ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተወሰኑትን የትራምፕ ማዕቀቦችን ለማቃለል ቃል ገብተዋል።

አርብ ዕለት በተካሄደው ኮንግረስ ላይ ራውል ካስትሮ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር "መከባበር ያለበት ውይይት ለማዳበር ፈቃደኛ መሆኗን" ገልፀው፤ ነገር ግን "የውጭ ፖሊሲዋን እና ሀሳቧን በተመለከተ ለውጥ ማድረግን" እንደማትቀበል ተናግረዋል።

ቀጥሎ ምን ይሆናል?

በኩባ አስተዳደር ፓርቲ አመራር ላይ የተደረገው ለውጥ ደሴቲቱ በአስርተ ዓመታት ውስጥ እጅግ አስከፊ የሆነውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም በምትሠራበት ወቅት ነው።

በትራምፕ አስተዳደር የተላለፈው ማዕቀብ፣ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢኮኖሚው ባለፈው ዓመት በ11 በመቶ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል።

በጥር 1 የተጀመረው እና ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የገንዘብ ማሻሻያ ኢኮኖሚውን እና የመንግሥት ኩባንያዎችን ውጤታማ ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም የኩባ ዜጎችን በጀት ጎድቷል።

ብዙዎችም በአገሪቱ የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ነፃነት እንዲኖር ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ሌላው ተግዳሮት በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን የዜጎችን የርዕዮተ ዓለም አንድነትና ድጋፋቸውን ጠብቆ ማስቀጠል ነው። በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ፀረ-መንግሥት ተቃውሞ በማሰማት እና በቀጥታ ሥርጭት ታዳሚዎችን በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ።

የአመራር ለውጥ ቢኖርም በፖሊሲ አቅጣጫው ላይ ለውጥ ያመጣል ብለው የሚጠብቁት ጥቂቶች ናቸው።

የ2019ቱ አዲስ ሕገ-መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት የበላይነት እና "ሶሻሊዝም" የማይቀለበስ መሆኑን አረጋግጧል።

የ60 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዲያዝ-ካኔል አርብ ዕለት ባሰፈሩት የትዊተር ጽሑፍ ጉባኤውን "ጠንካራ ሐሳቦች፣ የታሪክ እውቅና እና የወደፊቱ የሚወያዩበት ይሆናል" ብለዋል። ቀጣይነት እንደሚኖርም አክለው ገልጸዋል።

ራውል ካስትሮ በጉባኤው "መደበኛ አብዮታዊ ታጋይ" ተብለው ጡረታ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

"እናም በሕይወት እስካለሁ ድረስ የአባት አገርን፣ አብዮቱን እና ሶሻሊዝምን ለመከላከል በሚነሳው ችግር ውስጥ ለመግባት አገሬን አዘጋጃለሁ" ብለዋል።